በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሀገራችን ኢትዮጲያ አሁን ላይ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ውይይት በማካሄድ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል ። በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሀገርና ከህዝብ በላይ የሚያስቀድመው አጀንዳ ሊኖር ስለማይችል አሸባሪው የወያኔ ቡድንና ተላላኪዎች እየፈፀሙ ያለውን እኩይ ድርጊት አውግዘው ከህዝባቸውና ከመሪያቸው ጎን እንደሚቆሙም ገልፀዋል ።
ውድ ህይወቱን ሳይሰስት በግንባር ለሚፋለመው የመከላከያ ሰራዊትና የፀጥታ አካላት ያላቸውን አክብሮት ገልፀው ነዋሪው ህብረተሰብን በማስተባበርም በገንዘብ ፣ በአይነትና በግንባር የደጀንነት ተሳትፎ በጦርነቱ ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ በማሰባሰብ ከሰራዊቱ ጎን እንደሚሆኑም በጋራ መግለጫቸው ላይ አስታውቀዋል ።
የአስተዳደሩን ነዋሪዎች ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ከህዝባችን ጋር በመሰለፍ ጠላቶቻችን ተቀናጅተው የከፈቱብንን ጦርነት ለመመከት ነዋሪው ህብረተሰብ ከመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት እንዲጠብቅና ፀጉረ ልውጦችን በመከታተልና በማጋለጥ ከነዋሪው ህብረተሰብ የሚጠበቀውን ሚና አጠናክሮ እንዲወጣ በመቀስቀስና በማስተባበር ከመንግስት ጎን በመሆን የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ሀላፊነት እንደሚወጡም ገልፀዋል ።
ሁሉም የልማት ዘርፎች ሳይቋረጡ በመስራት ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር የመንግስት ሰራተኛው በየአገልግሎት ማእከሉ ህዝቡን ሳይታክት ማገልገል እንሚኖርበትና ስርቆትና የተደራጀ ዘረፋን በጋራ መታገል የፓርቲዎቹ የጋራ ተልእኮ እንደሆነና ነገር ግን ሀላፊነት የጎደላቸው ሰዎች ተደራጅተው ሀገራቸውን የሚሰርቁትን ሌቦች በጋራ እንደሚታገሉም አስታውቀዋል ። ከዚህ ባለፈም በሀገራችን ላይ በአሸባሪው ቡድን ፊት አውራሪነት እየተመራ በአለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማትና ግለሰቦች የሚደገፈው የሚዲያ በሬ ወለደ የስነ-ልቦና ጦርነት እውነትን እያዛባ እንደሚገኝና ይህንንም በጋራ በመከላከል አሸባሪው የሚያሰራጨውን የሀሰት መረጃ በማጋለጥ ለዜጎቻችንና ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ህዝባችንን ከጠላት የውሸት መረጃ ሰለባ እንዳይሆን የሚደረገውን ትግል አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉም ተናግረዋል ።
በተለያዩ የአለማችን ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጲያዊያን ትውልደ ኢትዮጲያዊ የዲያስፖራ ማህበረሰብ የጦርነት ሰለባ የሆነው ህዝባችንን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ርብርብ በገንዘብ ወገናችሁን ሊደግፍ እንደሚገባና በአሸባሪው የህወሀት ቡድንና በምእራባዊያን ሀገራት የተከፈተብንን ቅንጅታዊ ጦርነት በ no more እንቅስቃሴ ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ በማጋለጥ የጀመሩትን ገድል ለገና በአልም በሀገራቸው ኢትዮጲያ ተገኝተው በግንባር ሆነው ጥሪ ካደረገላቸው የሀገራችን መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጎን በመሆን እንዲደግሙት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጥሪውንም አቅርቧል ።


