በአሉን ተከትሎ በድሬዳዋ አስተዳደር ያለውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ፣ ታሪካዊ ቦታዎች እንዲሁም የከተማዋን ኢኮኖሚያ እድገት የሚያበለፅጉ የልማት ስራዎችን ከተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የመጡ ሀገር አቀፍ የሚዲያ አባላት ጉብኝት አካሂደዋል ። በሀገር አቀፍ ሚዲያ ባለሙያዎች ከተጎበኙ የልማት ድርጅቶች መካከል ለኢኮኖሚው እድገት አይነተኛ አስተዋፆ እየተወጣ የሚገኘው ሸሙ ፋብሪካ ይገኝበታል ።
ሸሙ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በ 1999 ዓ.ም ወደ ስራ የገባ ሲሆን ፋብሪካው ወደ ስራ ሲገባ ደረቅና ፈሳሽ የሳሙና ምርቶችን በማምረት የጀመረ ሲሆን ፋብሪካው አሁን ላይ ባለበት ደረጃም የሳሙና ጥሬ እቃ ፣ የተለያዩ ፕላስቲክ ፋብሪካ ፣ የህትመት ፋብሪካ ፣ የዘይት ፋብሪካና ተያያዥ ግብአቶች አሉት ።
ፋብሪካው የዛሬ 14 አመት በ 1 ሚልዮን ብር ካፒታል ስራ የጀመረ ሲሆን አሁን ላይ 385 ሚሊዮን ብር ካፒታል ላይ መድረስ ችሏል ። ይህም ካፒታል የፈሳሽ ሳሙናውን ፕሮጀክት ማጠቃለያውን ሳያካትት ሲሆን ይሄኛው የሚካተት ከሆነ ደግሞ ከ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ይዞ ነው እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ። ሸሙ ሀላፊነት የተወሰነ የግል ማህበር ከነዋሪው ህብረተሰብ እድገት አንፃር የተለያዩ የሳሙና ደረጃዎች ጥራታቸው ሳይጓደል ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደ ደረጃው የሚመረትበት አግባብ እንዳለና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠውን የዘይት ምርት ለማህበረሰቡ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ አምርቶ በማከፋፈል ላይ ይገኛል ።
ፋብሪካው አሁን ላይ 730 ቋሚ ሰራተኛ ከ 300 በላይ ደግሞ ቀን ሰራተኞች እየሰሩ ሲሆን የውጪ ምንዛሬን ከማስቀረት አኳያ ከዚህ ቀደም የሳሙና ጥሬ እቃ ከውጪ ይገባ ነበር አሁን ላይ ግን የዘይት ተረፈ ምርትን በመጠቀም ጥሬ እቃውን የማምረት ስራ በመሰራት ላይ ይገኛል ። ፋብሪካው በቀን የደረቅ ሳሙና 120 ቶን የማምረት አቅም ሲኖረው ፈሳሽ ሳሙና 60 ቶን ፣ ኑድልስ 120 ቶን ዘይት 900 ቶን በማምረት ላይ ይገኛል ።
ሸሙ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር 4 ፋብሪካዎች ያሉ ሲሆን ሌሎች ትልልቅ ፋብሪካዎች በአዲስ አበባና በዙሪያው ያሉት ሲሆን ይህም ፈጣን የሆነ እድገት በማሳየት ላይ ነው 50 ሺህ ካሬ ላይም ያረፈ ነው ።
ፋብሪካው ሀገራችን አሁን ላይ ላለችበት የህልውና ዘመቻ ይሆን ዘንድም 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረግ የቻለ ሲሆን በቀጣይም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ እቅድ እንዳለው የፋብሪካው ዋና ስራ-አስኪያጅ የሆኑት አቶ ተስፋ ሚካኤል ጉኡሽ አስታውቀዋል ።


