በሦስት ወራት ውስጥ ለሰብአዊ ድጋፎችና መልሶ ማቋቋም በአይነትና በገንዘብ 300 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ለማሰባሰብ ታቅዷል- የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

    በ3 ወራት ውስጥ በሚከናወን የሰብአዊ ድጋፎችና መልሶ የማቋቋም ስራ በአይነትና በገንዘብ 300 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ለማሰባሰብ እንደታቀደ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ፡፡
    ሚኒስትሯ ዛሬ በድሬዳዋ ከተማ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የወጣት አደረጃጀቶች የሰብአዊ ድጋፎችና መልሶ የማቋቋም ስራዎችን ለመስራት ከታህሳስ 1/2014 – የካቲት 30/2014 የሚከናወነውን ሀብት ማሰባሰብ ለማሳካት ሃገር ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናችን እንዲቆም እንጠይቃለን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
    ዶ/ር ኤርጎጌ ሀገሪቱ የገጠማትን የህልውና ጦርነት ለመመከት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ወጣቶች በህግ የማስከበር ዘመቻ ላይ በግንባር በመሰለፍ፣ በቅርብ ደጀን በመሆን፣ የአካባቢን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ፣ በመረጃና በኮሚዩኒኬሽን በመታገል፣ የዘማች ቤተሰቦችን በመንከባከብ፣ ሀብት በማሰባሰብና የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ ረገድ ታሪክ የማይረሳው አስተዋፅዖ በማበርከት ላይ ይገኛሉ ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡