ከጠላት ሃይል ጋር እያደረግነው ያለውን ዘመቻ በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ፊታችንን ወደ ልማት ማዞር ይኖርብናል ሲሉ የድሬዳዋ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም የሱፍ ተናገሩ፡፡
በአሸባሪው የህወኃት ቡድን የተቃጣብንን ጥቃት ለመመከት መላው ኢትዮጵያዊያን ከጫፍ ጫፍ በአንድነት ስሜት መትመማቸውን የገልጹት አቶ ኢብራሒም ዘመቻውን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅና በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ መገንባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
የጽ/ቤቱ ኃላፊ አያይዘውም ከውስጥም ከውጭም የተቃጣብንን ወረራ በጭር ጊዜ ቋጭተን ጠላቶቻችንን ሲደግሱልን የነበረውን ሴራቸውን አክሽፈን ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ሁሉም በየተሰማራበት የስራ መስክ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን በሉዓላዊነታችን ላይ ሲመጡብን ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን በማድረግና አንድነታችንን በማስቀደም አገርን ከጠላት መታደግ የቆዬና የነበረ ኢትዮጵያዊ መለያችን ነው ያሉት አቶ ኢብራሒም በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ላሳዩት የአገር ፍቅር ስሜትና አንድነት ያላቸውን አድናቆት ገልጸው የተፎካካሪ ፓርቲዎችም የፖለቲካ ልዩነቶቻችን ሳይገድቡን ከምንጊዜውም በላይ አገር ይቀድማል በሚል ከፍ ያለ ስሜት የእናት ጡት ነካሽ የሆነውን አሸባሪውን ቡድን በአንድነት ለመደምሰስ እያሳዩት ስላለው ተጋድሎ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በመጨረሻም በድሬዳዋ ሲካሄድ የቆየው 16ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን ለተወጡ የፀጥታ አካላትና የከተማው ነዋሪዎች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡


