አሸባሪው የህወሀት ቡድን በሀገራችን ኢትዮጲያ ላይ ግልፅ ጦርነት በማወጅ ሀገር የማተራመስና የማፍረስ ሴራውን በማካሄድ ላይ ይገኛል ። ይኸው አሸባሪ ቡድን በተለይም በአፋርና በአማራ ክልሎች ላይ ንፁሀን ዜጎቻችንን የመጨፍጨፍና ሀገር የማፍረስ ብሎም ዜጎችን የማፈናቀል ስራ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን ይህንንም የጥፋት ቡድኑን እኩይ ሴራ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመቅበር አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣት ይቻል ዘንድም ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከአማራና አፋር ልዩ ሀይልና ሚሊሻ ጋር እንዲሁም ከፀጥታ ሀይሎች ጋር በጋራ በመሆን አኩሪ ድል በማስመዝገብ ላይ ይገኛሉ ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በድሬዳዋ አስተዳደር ለሚገኘው የምስራቅ እዝ ደረጃ ሶስት ሪፈራል ሆስፒታል ግምታቸው ከ 700 ሺህ ብር በላይ የሆኑ የእርድ ከብቶች ፣ የንፅህና መጠበቂያ እቃዎች እንዲሁም የምግብ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል ።
በዚሁም የድጋፍ ስነ-ስርአት ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኡባህ አደም በተለይም ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ይሆን ዘንድ 10 ፐርሰንት ደሞዝና በድጋሚም የአንድ ወር ሙሉ ደሞዝ ከማዋጣት አንስቶ በተለያዩ ጊዜያቶች ደም በመለገስ ፣ ለሆስፒታሉ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጋቸውን ዶክተር ኡባህ አደም ተናግረዋል ።
ዶክተር ኡባህ አክለውም የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት በድሬዳዋ አስተዳደር ለሚገኙና በጦር ግንባር ጉዳት ደርሶባቸው በምስራቅ እዝ ደረጃ ሶስት ሪፈራል ሆስፒታል ለሚገኙ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት የሚሆኑ 10 በሬዎች ፣ ከ 14 ሺህ በላይ የንፅህና መጠበቂያ ሳሙናዎች ፣ ከ 10 ሺህ ሊትር በላይ ለልብስ ማጠቢያ የሚሆኑ ፈሳሽ ሳሙናዎችን ድጋፍ ማድረጋቸውን ዶክተር ኡባህ ተናግረው በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ሀገራችን ከገባችበት ጦርነት ወታ ሰላም ሰፍኖ ወደ ልማት ገብታ ብልፅግናዋን ለማረጋገጥ ትችል ዘንድም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉም ነው ዶክተር ኡባህ በድጋፍ ስነ-ስርአቱ ላይ የተናገሩት ።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ከሰራዊቱ ጎን እንደሆነና አሁን ላይም ላደረጉት ድጋፍ የምስራቅ እዝ ደረጃ ሶስት ሪፈራል ሆስፒታል ምክትል አዛዥ የሆኑት ኮረኔል ጌትነት አየነው አመስግነው የድሬዳዋ አስተዳደር እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች እያደረጉላቸው ላለው ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።


