በያዝነው አመት በድሬዳዋ አስተዳደር በቋሚና ጊዜያዊ ከ 17 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጠር ተገለፀ ።

    የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ባካሄደው 3 ተኛ የስራ ዘመን 1 ኛ አመት 7 ኛ አስቸኳይ ጉባኤ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር አስፈፃሚና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋምና ተግባርና ሀላፊነታቸውን ለመወሰን አዋጅ መውጣቱ ይታወቃል ። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በቀድሞ ስያሜው የድሬዳዋ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ የነበረው አሁን አዲስ በፀደቀው አዋጅ ላይ የአደረጃጀትና የስም ማስተካከያ ተደርጎበታል የድሬዳዋ አስተዳደር የስራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ በሚል ስያሜ በአዲስ መልኩ እንዲዋቀር ተደርጓል ።
    የድሬዳዋ አስተዳደር የስራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ በተለይም ከአደረጃጀት አንፃር ከዚህ ቀደም የነበረው የስራ እድል ፈጠራ ፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኤጀንሲ ፣ የልህቀት ማእከል ፣ በአዲስ መልክ የሚደራጀው የቴክኖሎጂ ኤጀንሲ እንዲሁም በቀድሞ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ኤጀንሲ ስር የነበረው ስራና ክህሎት ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ተጠሪ እንዲሆን እንደተደረገና እነዚህ ተቋማትም በቢሮው ስር እንደሚሆኑም የድሬዳዋ አስተዳደር የስራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሮቤል ጌታቸው ተናግረዋል ።
    አቶ ሮቤል ጌታቸው አክለውም ከስራ እድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ በድሬዳዋ አስተዳደር በያዝነው አመት ቋሚና ጊዜያዊ ከ 17 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጠርና በዚሁ የስራ እድል ፈጠራ ላይም በአብዛኛው ምሩቃንና ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚደረግም ገልፀዋል ። ከቴክኒክና ሞያ ጋር ተያይዞም ገበያ ተኮር የሆነ የቴክኒክና ሞያ ትምህርት ስልጠናዎች እንደሚሰጡና በዋናነትም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለህብረተሰቡ በማስተዋወቅ በአዳዲስ ዘርፍ ተፈላጊና ተመራጭ የሆነ የቴክኒክና ሞያ ትምህርት ስልጠና የሚሰጥበትን አግባብ በመከተል እንደሚሰራ አቶ ሮቤል ተናግረው በተለይም የምዘና ስርአትን ዘመናዊ በሆነ መልኩ የምዘና ማእከል ግንባታ እንደሚከናወንም ታውቋል ።
    ከዚህ በተጨማሪም በአዲሱ አደረጃጀት የመጣውን የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ በሀገራችን ላይ የወጡ ህጎችን በአግባቡ ተፈፃሚ የሚሆኑበትን አግባብ እንደሚፈጠርም አቶ ሮቤል ጌታቸው ተናግረው አዲሱ አደረጃጀት መፈጠሩም በራሱ ለነዋሪው ህብረተሰብ ፍትሀዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትና የመልካም አሰተዳደር ችግሮችን ከመፍታት አኳያ ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን እንደሚሰራ የድሬዳዋ አስተዳደር የስራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የሆኑት አቶ ሮቤል ጌታቸው ተናግረዋል ።
    የድሬዳዋ አስተዳደርን ልማትና እድገት ለማፋጠን ቴክኖሎጂ አይነተኛ አስተዋፆ እንደሚኖረው ይታመናል በዚህም መሰረት የድሬዳዋ አስተዳደር የስራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ለዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት አጠቃላይ የቴክኖሎጂና የኢኖቬሽን ስራዎችን በበላይነት የማስተባበር ፣ አዳዲስ ፈጠራዎች እንዲበረታቱ የማድረግ ፣ ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆንና ወጣቶችም በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ላይ እንዲሳቡም የተለያዩ የፈጠራ ውድድሮችን ከማዘጋጀት አንስቶ የቴክኖሎጂ ካፌና ፓርኮችን ለመስራት መታቀዱንም ነው አቶ ሮቤል ጌታቸው ያስታወቁት ።