የእናታቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት የገቡትና በድሬዳዋ ተወላጅ የሆኑት ወገን ወሰን፣ አደላሽ ክፍሌ፣ እና ስንታየሁ አርጋው፤ ዛሬ ድሬዳዋ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
በከንቲባው ጽ/ቤት የዳያስፖራ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አቤል አሸብር እንግዶቹን በተቀበሉበት ስነ-ስርዓት ላይ፤ በድሬዳዋ የተለያዩ ቀበሌዎች የሚገኙ ታዳጊ እግር ኳስ ቡድኖች ተጫዋችና አሰልጣኞቻቸው ተገኝተው፤ የእንኳን ደህና መጣችሁ አበባ በማበርከት ምስጋና፣ ፍቅርና አክብሮታቸውን ገልፀዋል።
እኚህ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወንድምና እህቶች፤ ከዚህ ቀደም በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የታዳጊ እግር ኳስ ቡድኖችን፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት ማቆያ ማዕከልን፤ የመማሪያ ቁሳቁስ ማሟላት የማይችሉ ተማሪዎችን በማገዝ፤ እንዲሁም የወገናቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመቅረፍ በሚከናወኑ በርካታ የድጋፍ ተግባራት ላይ ግንባር ቀደም ተሳትፎ በማድረግ ይታወቃሉ።
በአሁኑ ወቅትም በአስተዳደሩ ለሚገኙ አቅመ ደካማ ነዋሪዎች የሚውል፤ የኩላሊት ህክምና እጥበት መሳሪያ ለመግዛት የተጀመረውን የገንዘብ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ እያስተባበሩ ሲሆን፤ አንዱ ገበታ በ10,000 ብር እየተሸጠ በሚገኘው የድሬዳዋ የክብር እራት ፕሮግራም ላይ ለመሳተፍ ወደ ትውልድ ከተማቸው እንደመጡ ታውቋል።
ከቀናት በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ ተቀብለው ከውጭ ሀገራት የመጡና፤ ወደ ትውልድ ከተማቸው ድሬዳዋ የገቡ በርካታ የዳያስፖራ አባላትን ያሳተፈ፤ በአስተዳደሩ የቀረቡ የተለያዩ አዋጭ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ያተኮረ ሲምፖዚየም መካሄዱም ይታወሳል።


