በድሬዳዋ አስተዳደር የተከበረው የጥምቀት በአል ፍፁም ሰላማዊ በሆነ አግባብ መከበሩ ተገለፀ ።

    በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበረው የጥምቀት በአል በድሬዳዋ አስተዳደርም ተከብሯል ። በተለይም በአሉ በድሬዳዋ አስተዳደር ሲከበር በርካታ የእምነቱ ተከታዮች ከጥምቀት ከተራ በአል አንስቶ ታቦታቱ ከመንበራቸው ወተው በክርስትና እምነት ተከታዮች ዝማሬና እልልታ ታጅቦ በጥምቀተ ባህር ካደሩ በኋላ በጥምቀት በአል ቀን ታቦታቱ ወደ ደብራቸው በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በእልልታና በዝማሬ አጅበው በሰላም አስገብተዋል ።
    ከዚሁ የበአል አከባበር ጋር ተያይዞ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ እንዲሁም የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መላከ ሀይል አባ ተስፋዬ እማምሰው በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል ።
    የጥምቀት በአልን ከባለፈው አመት ለየት ባለ መልኩ ይከበር ዘንድ በአሉ በሰላም ተጀምሮ ይጠንቀቅ ዘንድ የሀገረ ስብከት ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤትና ምእመናን ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ፣ የፌደራል ፖሊስ ፣ የመከላከያ ሰራዊት ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፆ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ምስጋናቸውን አቅርበው በተለይም የፀጥታውን አካል በበላይነት ሲመራ የነበረው የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ እንዲሁም የምስራቅ ፌደራል ፖሊስ ኮማንደር ሰለሞን ከመከላከያ ሻምበል ጥላሁን በአሉ በሰላም ተከብሮ ይጠንቀቅ ዘንድ በጋራ በመሆን ላሳዩት አስተዋፆ ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሀር ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።
    አቶ ከድር ጁሀር አክለውም በድሬዳዋ አስተዳደር የሚኖሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ለክርስትና እምነት ተከታዮች በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ላይ የተለያዩ ምግቦችንና የታሸጉ ውሀዎችን በማቅረብና በመስጠት በአሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ላደረጉት አስተዋፆ አቶ ከድር ጁሀር ምስጋናቸውን አቅርበው የህብረ-ብሄራዊ አንድነት ፣ የመቻቻል ከተማ ፣ የፍቅር ተምሳሌት የሆነችው ከተማችን ድሬዳዋ በተግባር የህዝብ ፍቅርና አንድነት በማሳየት የፀጥታ አካላትን አረጋዊያንን ህፃናትን በማገዘና በመርዳት በአሉ ስኬታማ በሆነ መልኩ እንዲከበር ማስቻሉንም ክቡር ከንቲባው አስታውቀዋል ።
    ከጥምቀት በአሉ ጋር ተያይዞ ታቦታቱ ሲወጡና ሲገቡ ቄጣማዎች መጎዝጎዛቸውን ተከትሎ በነገው እለት ጠዋት በሚካሄደው የፅዳት ዘመቻ ላይ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በፅዳት ዘመቻው ላይ ተሳታፊ በመሆንና ታቦታቱ ባለፍባቸው አካባቢዎች ላይ የፅዳት ዘመቻዎችን በማካሄድ የከተማዋን ፅዳት ማስጠበቅ እንደሚገባም ነው ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ጥሪያቸውን ያቀረቡት ።
    እንደሚታወቀው በሀገራችን ኢትዮጲያ በአደባባይ ከሚከበሩት በአላት አንዱ የጥምቀት በአል ነው ። ይሄም በአል በድሬዳዋ አስተዳደር ሲከበር የድሬዳዋ የጋራ ጥምር የፀጥታ ሀይሎች ማለትም የድሬዳዋ ፖሊስ ፣ የፌደራል ፖሊስ ፣ የሀገር መከላከያ ፣ ብሄራዊ ደህንነት ፣ የፀጥታ ቢሮ በጋራ በመሆንና በክቡር ከንቲባው የበላይ መሪነት እቅድ ወቶ በአሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር ሊከናወን መቻሉን የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ ተናግረዋል ።
    ለዚህም ስኬት ዋንኛውን ሚና የሚይዘው የፀጥታ ሀይሉ እንዳለ ሆኖ በተለይም በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ ወጣቶች መንግስት ያወጣውን መመሪያ ስራ ላይ በመተግበር ድሬዳዋ ከዚህ ቀደም በተሻለ መልኩ ሰላሟን ያረጋገጠችበት በአል እንደነበረም ኮሚሽነር አለሙ መግራ ተናግረው በድሬዳዋ አስተዳደር የሚኖሩ የእስልምና እምነት ተከታዮችም በአሉ የኛም በአል ነው በማለት የተለያዩ ምግቦችንና ውሀዎችን ከማዘጋጀት አንስቶ ፀጥታውን ከወንድሞቻቸው ጋር በጋራ በመሆን በማስጠበቅና በማክበር ፍፁም ልዩ የሆነ በአል ሊከበር መቻሉንም ነው ኮሚሽነር አለሙ መግራ የተናገሩት ።
    የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መላከ ሀይል አባ ተስፋዬ እማምሰው በበኩላቸው በአሉ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ አግባብ መከበሩንና ለዚህም መሳካት ከፍተኛውን ሚና ለተወጡት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በተለይም በአሉ ከመከበሩ 15 ቀን ቀድም ብሎ በአሉ የሚከበረበትን ቦታዎች ከማፅዳትና አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ከማስተካከል አንስቶ ላደረጉት አስተዋፆ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።
    የፀጥታ አካላትም በአሉ ሰላማዊ እንዲሆን ከፍተኛ የሆነ አስተዋፆ እንዳበረከቱና ለዚህም የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ መመሪያ ከመስጠት አንስቶ በአሉ የሚከበርባቸው ቦታዎች ላይ በመገኘት በአሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ስራ እንደሰሩና የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎችም ላደረጉት አስተዋፆ የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መላከ ሀይል አባ ተስፋዬ እማምሰው ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።