ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በድሬዳዋ አስተዳደር እየተስተዋለ ያለውን ከፍተኛ የሆነ የሲሚንቶ ዋጋ ጭማሪ ብሎም የአቅርቦት ችግር ለመፍታት ይቻል ዘንድ ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር በቅርበት በመሆን በመስራት ላይ የሚገኝ ሲሆን ነገር ግን አንድ አንድ ቸርቻሪዎች በአጭር ለመበልፀግ በማበለም በህገ-ወጥ የሲሚንቶ ንግድ ላይ በመሰማራት የሲሚንቶ ውድነትና አቅርቦት እጥረት ችግር እንዲከሰት እያደረጉት ይገኛሉ ።
የአስተዳደሩ የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮም ባደረገው ጥብቅ የሆነ የክትትልና ቁጥጥር ስራም ባሳለፍነው አርብ ምሽት በህገ ወጥ መንገድ ሊሸጡ የነበሩ 600 ኩንታል ሲሚንቶ የጫኑ 5 መኪናዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል በትናንትናው እለትም በተደረገው ቁጥጥርም ማምሻዉን ከከተማዋ በህገ-ወጥ መንገድ ሊወጣ የነበረ 5 ኤፍ ኤ ሳርና 1 ከባድ ተሽከርካሪ እስከነ ተሣቢዉ ሲሚንቶ በጫነበት በቁጥጥር ስር ማዋሉን የድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ እንድስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊና የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ልማት ኤጀንሲ ሀላፊ የሆኑት አቶ አብዲ ሙክታር አስታዉቀዋል ።
አቶ አብዲ ሙክታር አክለውም በከተማዋ ላይ የሚገኙ ስግብግብ ነጋዴዎች ሲሚንቶን አየር በአየር አየሸጡ ህዝቡን በከፍተኛ ሁኔታ ማማረራቸዉን ተናግረው 1 ኩንታል ሲሚንቶ በተተመነለት 580 ብር ከ 36 ሳንቲም መሸጥ እንደሚገባዉ አስገንዝበዋል ። በተለይም ቢሮዉ የሲሚንቶን ዋጋ ለማረጋጋት የተለያዩ ስልቶችን በቀጣይነት ነድፎ እንደሚንቀሳቀስና ለዚህ እንቅስቃሴም መሳካት ነዋሪው ህብረተሰብ ከጎናቸዉ እንዲቆምም ነው አቶ አብዲ ሙክታር ጥሪያቸዉን ያስተላለፍት።


