በድሬዳዋ አስተዳደር እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ሊጠናቀቁ እንደሚገባ ተገለፀ ።

    በ 2014 በጀት አመት በድሬዳዋ አስተዳደር ማለቅ የነበረባቸው የመንግስት ፕሮጀክቶች አፈፃፀማቸው ላይ መዘግየቶች እየተስተዋሉ ሲሆን እነዚህም ፕሮጀክቶች ያልተጠናቀቁበትን ምክንያት በመለየት የሚጠናቀቁበት ሁኔታ ላይ የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ይቻል ዘንድ ከኮንትራክተሮች ፣ ከግንባታ ባለቤቶች እንዲሁም ከግብአት አቅራቢዎች ጋር በዛሬው እለት ውይይት ተካሂዷል።

    በውይይቱ ላይም ኮንትራክተሮች በስራቸው ላይ አሉ ያሉትን ችግሮች ያነሱ ሲሆን በተለይም የዲዛይን ችግር ፣ የሲሚንቶ አቅርቦት ችግር ፣ የበጀት እጥረት እንዲሁም የግንባታ እቃዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ መናር ግንባታዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ በእጅጉ የተቸገሩበት ጉዳዮች መሆናቸውን ኮንትራክተሮቹ ተናግረዋል ።
    በድሬዳዋ አስተዳደር እየተገነቡ ባሉ ፕሮጀክቶች ላይ ጥሩ አፈፃፀም ያላቸውን ኮንትራክተሮችን እያበረታቱ ነገር ግን ክፍተት ያለባቸውን ኮንትራክተሮች በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ተናግረው በከተማው ላይ ሁለት ሲሚንቶ ፋብሪካዎች እያሉ የሲሚንቶ አቅርቦት ችግር ሊገጥም እንደማይገባና በቀጣይም የአቅርቦት ችግሮች እንዳይኖሩ በትኩረት እንደሚሰራ ክቡር ከንቲባው ተናግረዋል።
    ከግንባታ ጋር ተያይዞ ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ የሲሚንቶና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶበት በመሰራት ላይ እንደሆነ የድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ኢንጂነር ጀማል ኢብራሂም ተናግረው ኮንትራክተሮች ጋርም የሚታዩትን ክፍተቶች ማሻሻል እንደሚገባና በቀጣይም ያነሷቸው ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራም ነው ኢንጂነር ጀማል ኢብራሂም በእለቱ የተናገሩት ።
    በውይይት መድረኩ ላይም ኮንትራክተሮች ፣ የግንባታ ባለቤቶች ፣ የግብአት አቅራቢዎች እንዲሁም ከፍተኛ የአስተዳደሩ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል ።