የሲቪክ ማህበራት ነዋሪውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን መስራት እንደሚገባቸው ተገለፀ ።

    በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ ሲቪክ ማህበራት የ 90 ቀናት እቅድ አፈፃፀም ላይ ከነዋሪው ህብረተሰብ ጋር ውይይት አድርገዋል ።
    በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙና መንግስታዊ ያልሆኑ የሲቪክ ማህበራት በከተማው ላይ በተለያዩ የማህበራዊ እንዲሁም የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊ ሆነው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ ሲሆን እነዚህም ሲቪክ ማህበራት በተለይም በማህበራዊም ሆነ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ እየሰሩት ያሉትን ስራዎች ብሎም መንግስት ባስቀመጠው የ 90 ቀናት እቅድ አቅጣጫ መሰረት እየሰሩ ባሉት ስራዎች ዙሪያ ለመወያየትና የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ይቻል ዘንድ በዛሬው እለት የገፅ ለገፅ ውይይት ተደርጓል ።
    በዚሁም ውይይት ላይ ከተሳታፊዎች ሀሳብ አስተያየት የተሰጠ ሲሆን በተለይም የሲቪክ ማህበራት ስራቸውን ለነዋሪው ህብረተሰብ ተደራሽ ከማድረግ አንፃር ክፍተቶች እንዳሉ ፣ መንግስት ለሲቪክ ማህበራት የሚያደርገው ድጋፍ አነስተኛ መሆኑን እንዲሁም በከተማው ላይ 42 የሚሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዳሉ ቢታወቅም ነገር ግን ፕሮጀክት ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ያሉት 34 የሚሆኑ ድርጅቶች መኖራቸውን ገልፀዋል ።
    በከተማው ላይ ፕሮጀክት ነድፈው ለህብረተሰቡ የማይሰሩ ሲቪክ ማህበራት ላይ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን መስራት እንዳለባቸው እንዲሁም ሲቪክ ማህበራት ነዋሪውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች ላይ አትኩረዉ መስራት እንዳለባቸው የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የመረጃ አካላትና ማብቃት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ብርሀኑ ሀብተወልድ ዲሌሞ የገለጹ ሲሆን ሲቪክ ማኀበራት መንግስት የህብረተሰቡን መህበራዊ ችግሮች ለመፍታት የሚያደርገዉን ጥረት በማገዝ የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በማቃለል ተጠቃሚነታቸዉን ለማረጋገጥ የሚያደርጉት ጥረት አበረታች ነዉ ያሉት ደግሞ የመንግስት ኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሙአዝ አሊ ሲሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶች የፕሮጀክት እቅዶቻቸዉን ወደ ህብረተሰቡ በመዉረድ የህዝብን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ስራ መሰራት እንዳለባቸዉ ነዉ የገለጹት ።