የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ በ03 ቀበሌ ድንገተኛ ጉብኝት አደረጉ፡፡

    በድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በዚህም የከተማ ቀበሌዎች ለህብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት ጥራት ያለው እና ቀልጣፋ እንዲሆን የሚያስችለውን ሪብራንዲንግ የተሰኘ ፅንሰ ሀሳብ እንዲተገብሩ መደረጉ ይታወቃል፡፡
    በዚህም በአስተዳደር ደረጃ ያሉ ቀበሌዎች ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት ተገምግመው ደረጃ የወጣላቸው ሲሆን ያገኙትን ውጤት መሰረት በማድረግም ለሶስት የከተማ ቀበሌዎች ማለትም 03፣04 እና 09 ቀበሌዎች ልዩ ድጋፍ እንዲደረግላቸው እና ሞዴል መሆን በሚችሉበት ደረጃ እንዲለወጡ አስተዳደሩ አቅጣጫ አስቀምጦ እየተሰራ ይገኛል፡፡
    የተቀመጠውን አቅጣጫ መሰረት በማድረግ ተቋማቱ የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማሻሻል እየሰሩ ያሉትን ስራዎች በተግባር ለማየት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ ከድሬዳዋ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ አመራሮች እና ባለሞያዎች ጋር በመሆን በ03 ቀበሌ ድንገተኛ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
    ባደረጉት ጉብኝትም በቀበሌው ያሉ ሁሉንም ማስተባበሪያዎች ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን በምልከታቸውም የቀበሌው አመራሮች እና ሠራተኞች ለህብረተሰቡ የሚሰጡት አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸሻለ መምጣቱንም ነው አቶ ሀርቢ የገለፁት፡፡
    በአጠቃላይ በቀበሌው ከስራ ሰዓት አከባበር፣ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲሁም በአመራሩ እና በባለሞያዎች ዘንድ የአገልጋይነት መንፈስል ተላብሶ በደስታ ህብረተሰብን ከማገልገል አንፃር ለሌሎችም ምሳሌ የሚሆን የአገልግሎት አሰጣጥን ማየታቸውን የገለፁት አቶ ሀርቢ የሚታዩ ክፍተቶችን በማረም በቀጣይ ከዚህ የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖራቸው ሊሰሩ እንደሙገባም ተናግረዋል፡፡
    አቶ ሀርቢ አክለውም እንደ አስተዳደር የመንግስት ተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል በ10 የተመረጡ ተቋማት ላይ እየተሰራ ያለው ሪፎርም በ3ቱ ቀበሌዎችም ላይ እንዲተገበር እንደአስተዳደር አቅጣጫ መቀመጡን ገልፀው የ03 ቀበሌም ይህንኑ ለመተግበር ከድሬዳዋ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ የሪፎርም ቴክኒካል ኮሚቴ በሚደረግላቸው ድጋፍ እና ክትትል መሰረት በአጭር ጊዜ ወደ ሪፎርሙ እንዲገቡም አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡