የ‘ተረኝነት’ ጉዳይን በተመለከት

    ሀገራችን ለሁላችንም የሚበቃ ሀብት አላት። የተፈጥሮ፣ የታሪክ፣ የባህል እና ከምንም በላይ የጊዜ ሀብት አለን። ይህን ሰብስቦ ለጥቅም ማዋል ሲቻል፣ ሀገርን እንደ እቁብ አይቶ በዚህኛው ቀን ለእከሌ፣ በሌላ ቀን ለእከሌ በፈረቃ የምትደርስ ያደርጋታል። እንኳን ለሀገር፣ ለመብራትም ፈረቃ ይከብዳል። ሀገር የምትመራው በጋራ ነው። ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓም፣ ሕግ አስፈጻሚ እና ርዕሰ ብሔር የሀገረ መንግሥቱ ምሰሶዎች ናቸው።
    በሲቪል ሰርቪስ በተደረገው ቆጠራ አማካኝነት በመንግሥት አስተዳደር የብሔር ተዋጽኦ ሁሉን አቀፍ መሆኑን፣ በፌደራል ሠራተኞች ደረጃም ጭምር አይተናል። የልማት ድርጅቶችም ተፈትሸዋል። ለምሳሌ፦ አየር መንገድ የሥራ አስፈጻሚው 74 በመቶ አማራ፣ 5 በመቶ ትግሬ፣ 5 በመቶ ኦሮሞ ቀሪውን የተለያዩ ብሄሮች የተውጣጡበት ነው። አየር መንገዱ በውጪም ያካተተው አስፈጻሚ 52 በመቶ አማራ፣ 16 በመቶ ኦሮሞ፣ 15 በመቶ ትግሬ ቀሪውን የተለያዩ ብሄሮች የተውጣጡበት ነው።
    ምክር ቤቱ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ወስዶ የብሔር፣ የጾታ፣ የእምነት እና የመሳሰለውን ተዋጽዖን የተመለከተ ሕግ አውጥቶ በዚያ መሠረት ቢያስፈጽም የሚነሳውን ጥያቄ ሁሉ በሚገባ ይቀርፈዋል።
    የምናነሳው ሀሳብ ሁሉ በእውነታ እንጂ በተረት ላይ የተመሰረት አይሁን።