ዝርዝር ዜና
በገር አቀፍ ደረጃ የመጣውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ ተከትሎ የመንግስት አገልግሎት ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር፤ ብሎም ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ፤ የመንግስት አገልግሎቶች ፈጣን ቀልጣፋ እና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል በተለያዩ አስር ተቋማት ላይ የሪፎርም ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ትላንት በአስተዳደሩ ከንቲባ አዳራሽ በስድስት ተቋማት ላይ የሪፎርም ስራ አተገባበራቸውን በተመለከተ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ከነዚህም ተቋማት ውስጥ የድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ይገኝበታል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ አብዲ ሙክታር ሪፖርቱን ያቀረቡ ሲሆን ተቋሙን በአራት ዘርፍ ሪፎርሙን እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አደረጃጀት፣ አሰራር፣ የሰው ሀይል ጋር በተያያዘ እንዲሁም ቴክኖሎጂን በተመለከተ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የመንግስት የስራ መግቢያ እና የመውጫ ሰዓትን እራስን እስካን የሚያደርግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሶፍትዌር፣ ደምወዝን ጨምሮ የነዳጅ ቅጂን ለማዘመን በኤቲየም የተደገፈ አሰራር ለመስራት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ የስራ ቦታን ምቹ ከማድረግ አኳያ የካይዘን ትግበራ በተቋማቸው ውስጥ እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ አብዲ ገልፀዋል፡፡
ቀጣይ የሪፎርም አተገባበሩን ያቀረበው የብዙሀን መገናኛ ድርጅት ሲሆን ተቋሙ ከግንቦት 16 ጀምሮ ባዘጋጀው የሪፎርም እቅድ መሰረት የተከናወኑ ስራዎችን አቅርቧል፡፡ ሪፖረቱን ያቀረቡት የብዙሀን መገናኛ ድርጅት ሀላፊ የሆኑት አቶ ሱሌማን አሊ ሲሆኑ የሰው ሀይል ላይ ከ8ተኛ ክፍል እስከ ዲግሪ ያሉ 158 ሰራተኞችን የፎርጂድ ወረቀት የማጥራት ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ 55 ሰራተኞች ላይ የትምህርት ማስረጃቸውን ይበልጥ በመከታተል የሰራተኛ ማህደራቸውን አገላብጠን ጡረታ የወጣ ሰራተኛ እየሰራ ማግኘታቸውን አብራርተዋል፡፡ ብልሹ አሰራር የተከተሉ ሁለት ሰራተኞችን የማሰናበት ስራ በዚህ የሪፎርም ትግበራ ወስጥ መፈፀማቸውን አቶ ሱሌማን ተናግረዋል፡፡
የተቋሙን የደንብ ማሻሻያ ቀሪ ስራች መኖራቻን የጠቀሱት አቶ ሱሌማን ከ28 መመሪያዎች 18 የፀደቁ ሲሆን ባልፀደቁት መመሪያዎች ላይ የማሻሻል እና የማስተካከል ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ የሰራተኛውን ልምድ ከማጎልበት አንፃር ፋና እና የኦሮሚያ ሚዲያ የልምድ ልውውጥ በማድረግ ልምዶቹን ቀምረን ወደ ተቋማችን በማምጣት ለመስራት ችለናል ብለዋል፡፡
የስራ ቦታን ምቹ ከማድረግ አኳያ ሁለቱን የሬዲዮ እና የቴሌቭዥን ስቱዲዮዎችን ለአድማጭ ተመልካች ምቹ እንዲሆን የማስተካከል ስራ መሰራቱን የብዙሀን መገናኛ ድርጅት ሀላፊ የሆኑት አቶ ሱሌማን አሊ ተናግረዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱሰላም መሀመድ የተቋማቸውን የሪፎርም ስራዎች ትግበራ በሪፖርታቸው አቅርበዋል፡፡
ገቢዎች ባለስልጣን በዋናነት አቅዶት የተነሳው አስተዳደሩ እራሱን በገቢ እንዲችልና ወቅቱን ያገናዘበ የሚመጥን አደረጃጀት ያለው ተቋም የመገንባት ስራ በሰው ሀይል፣ በአቅርቦት፣ በአሰራር ጭምር የማስተካከል ስራ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
በዋናነት ከሰራተኛው እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ለተቋሙ ሪፎርም ያስፈልገዋል ወይንስ አያስፈልገውም የሚለውን ሀሳብ በማቅረብ ያስፈልጋል በሚል ተግባብተን ነው ወደ ሪፎርም የገባነው ብለዋል፡፡
በዚህም የተለያዩ አሰራርና ህግ የሚለዩ ኮሚቴ አቋቁመናል፣ የግብር ስርዓቱ መዘመን እንዳለበት የገለፁት ዳይሬክተሩ ቴክኖሎጂውን የሚደግፍ ኮሚቴ የተዋቀረ ሲሆን፣ የሰው ሀይል የሚያጠራ የሰነድ ጥራት ከሰው ሀይል ቅጥርና ስንብት ጋር በተያያዘ የሚገመግም ኮሚቴ በበላይነት የሚያስተባብር አዘጋጅተን ወደ ስራ ገብተናል ብለዋል፡፡
በዚህም በጣም ከፍተኛ ለውጥ ተመዝግቧል ያሉት አቶ አብዱሰላም ተቋሙን ለተገልጋዮች እና ለሰራተኞች ምቹ የማድረግ ስራዎችን በሪፎርሙ የጀመርንበት ሁኔታ ነው ያለው ብለዋል፡፡ በሪፎርሙ ከፍተኛ ለውጥ ያገኘንበትና ግብር ከፋዮቻችን ላይ ከፍተኛ እርካታ የፈጠረ እንዲሁም ሰራተኞቻችንም ላይ ውጤታማ ያደረገ ያደረገ ሪፎርም ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ሪፎርም የግብር ስርዓታችን እንደ አስተዳደር ወደ ተሸለ ደረጃ ምናሸጋግርበት ሁኔታ ይፈጠራል፣ ለግብር ስርዓቱ መዘመን የሚዲያ አካላት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ማህበረሰባችንም በግብር አከፋፈል ዙሪያ አሁን ያለውን ተነሳሽነት እንዲቀጥልና በተለይ አገልግሎት ሲያገኝ ላገኘበት አገልግሎት ደረሰኝ የመጠየቅ ባህል የማዳበር ስራ ተቋሙን እንዲደግፍ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ቀጣይ የድሬዳዋ አስተዳደር መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የሪፎርም አተገባበሩን ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን ቢሮው እራሱን ሪፎርም ለማድረግ እቅድ አቅዶ እቅዱን ወደመተግበር የገባበት ሁኔታ መኖሩን የቢሮው ተወካይ የሆኑት አቶ ሙአዝ አሊ ተናግረዋል፡፡
ቢሮው አራት ኮሚቴዎች ለሪፎርሙ ያዋቀረ ሲሆን የአደረጃጀትና የአሰራር ንዑስ ኮሚቴ፣ የለውጥ ስራ እና የመልካም አስተዳደር ንዑስ ኮሚቴ፣ የቴክኖሎጂና የግብዓት ዝግጅት ንዑስ ኮሚቴ እንዲሁም እነሱን የሚያስተባብር አብይ ኮሚቴ መኖሩን አቶ ሙአዝ አንስተዋል፡፡
ቢሮው ያለውን የሰው ሀይል የማጠናከርና አቅሙን በአግባቡ የመጠቀም የአደረጃጀት ስራ በሪፎርሙ ይሰራል ብለዋል፡፡ ለቢሮው የተለያዩ ግብዓቶች ያስፈልገዋል ያሉት የቢሮው ተወካይ አቶ ሙአዝ ቴክኖሎጂን የተከተለ አሰራር እንዲኖረው በርካታ ሲስተም በሪፎርሙ የመዘርጋት እቅድ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ እስከ ቀበሌ ድረስ ያለውን የኮሙዩኒኬሽን ስራ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ በሚችል አኳኋን የሚሰራበት ሲስተም እንደሚዘረጋና ቢሮው የራሱን ተልዕኮ በአግባቡ መወጣት የሚችልበት ሁኔታ በሪፎርሙ እንደሚፈጠር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ ተወካይ የሆኑት አቶ ሙአዝ አሊ ተናግረዋ፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር የፍትህ፣ ፀጥታና የህግ ጉዳዮች ቢሮ የሪፎርም ስራዎች አፈጻፀም ሪፖርት በተመለከተ በትላንትናው መድረክ ቀርቧል፡፡ የፀጥታና የሰላም ማረጋገጥ እንዲሁም የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን በአንድ ላይ እየሰራ አገራዊ እና አስተዳደራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ የተቋሙ ሀላፊ አቶ አብዱሰላም አህመድ ተናግረዋል፡፡
የፍትህ፣ ፀጥታና የህግ ጉዳዮች የተለያዩ ስራዎችን የያዘ ተቋም ሲሆን አደረጃጀት ተፈጥሮላቸው ሊመሩ የሚገባቸው ተቋም ናቸው ብለዋል፡፡ አንድ ላይ አጣምሮ መያዙ ከሁለቱ ዘርፎች የሚጠበቁ ውጤቶች በሚፈለገው ደረጃ እንዳይወጡ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ተቋሙ ባለፉት ዓመታት በጣም ከተዘነጋ የአስተዳደሩ ተቋም ቀዳሚ ነው ያሉት አቶ አብዱሰላም ስራው ትልቅ ቢሆንም የተሰጠው ትኩረት አናሳ ነው፡፡ አሁን ላይ የሪፎርሙ አካል በመሆናችን በጣም ተጠቃሚ ያደርገናል ብለዋል፡፡
የፍትህ፣ ፀጥታና የህግ ጉዳዮች ቢሮ በሚል ስያሜ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው ተቋም ወደ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ እንዲሁም የፍትህ ፅ/ቤት በሚል ስያሜ ተነጥለው እንዲደራጁ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተቋማቱን ለማደራጀት በሪፎርሙ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አቶ አብዱሰላም ተናግረዋል፡፡
ሪፎርሙ የሚመራበት የማስተግበሪያ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን የፍትህ፣ ፀጥታና የህግ ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ አብዱሰላም አህመድ ገልፀዋል፡፡
የቢሮ የሪፎርም ስራዎች ለማስፈፀም የሚረዱ ሶስት ንዑሳን ኮሚቴዎች እንዲቋቋም የተደረገ ሲሆን በአደረጃጀት የሰው ሀይልና የህግ ማዕቀፍ ዝግጅት ንዑስ ኮሚቴ፣ የለውጥ ስራዎችና የኮሚኒኬሽን ስራዎች አስተግባሪ ንዑስ ኮሚቴ፣ የግብዓት አቅርቦትና የስራ ቦታ ምችችት ንዑስ ኮሚቴ ማቋቋማቸውን የቢሮው ሀላፊ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም የሪፎርሙን ሪፖርት ያቀረቡት የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ ናቸው እንደ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ ገለጻ ከሆነ እኛም እንደ ጤና ቢሮ በጤና ተቋማት፣ በሆስፒታል፣ በጤና ኬላ፣ እንዲሁም በጤና ጣቢያ ላይ ያለውን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል የአሰራር ለውጥ ዘርግተን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
ሪፎርሙ በዋናነት ያስፈለገበት ምክንያት የጤና ቢሮ አገልግሎት አሰጣጡ ማህበረሰቡ በአግባቡ አገልግሎት እያገኘ እንዳልሆነ በተለያዩ መድረኮች በመነሳቱ ነው ያሉት ወ/ሮ ለምለም ይህን መነሻ በማድረግ ለውጥ ያስፈልገናል ብለን እራሳችንን ፈትሸናል፡፡
የአሰራር ለውጡ በሰው ሀይል አደረጃጀት ማነቆ የሆኑ መመሪያዎችና አዋጆችን በማየት ከቴክኖሎጂ አንጻር በምን አይነት ቴክኖሎጂ የጤናው ዘርፍ መታገዝ አለብን የሚለውን አምስት ኮሚቴ አዋቅረን ፈትሸናል ብለዋል፡፡
የማህበረሰባችን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጠቱ በድልጮራ ሆስፒታልና በጤና ጣቢያዎቻችን ላይ የተገልጋይ ቁጥር ጨምሯል የሰራተኞቻችን ቁጥር እዛው ባለበት ነው ያለው ያሉት ወ/ሮ ለምለም በዚህ ሪፎርም ላይ በስፋት የምናየው ይሆናል ብለዋል፡፡
በስነ ምግባር የታነፀ የጤና ባለሞያ እንዴት መፍጠር እንችላለን፣ የጤና ባለሙያዎች በሰዓቱ ተገኝተው ተገልጋዩን እንዴት ማስተናገድ ይችላሉ፣ ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ በምሽት የስራ ጊዜያቸው እንዴተ እየሰሩ ነው ያሉት የሚለውን በደንብ እየፈተሽን እንገኛለን ብለዋል፡፡
በቀረቡት የሪፎርም ሪፖርቶች ላይ ሀሳባቸውን የገለፁት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ክቡር ሀርቢ ቡህ ከሞላጎደል ሌሎች ተደራቢ ስራ እየሰራቹ ያቀረባቹት የሪፎርም የሪፖርት ስራ ጥሩ ጅምር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ቀጣይ ሁሉም ሪፎርም ላይ ያሉ ተቋማቶች ወጥ በሆነ መልኩ መሄድ እንዳለባቸው በምክትል ከንቲባው የስራ አቅጣጫ ተቀምጦ በቀረቡት የሪፎርም ሪፖርቶች ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን መስተካከል በሚገባቸው ነገሮች ላይ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡


