ፎረም ኦን ሰስተኔብል ችልድረን ኢምፓውርመንት ከዚህ ቀደም በህፃናት ትምህርትና ጤና ላይ ይሰራ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ደግሞ ከህፃናቱ ባለፈ ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግና ለአምስት አመት የሚቆይ ” ከፍታ ” የሚል ፕሮጀክት በመቅረፅ በድሬዳዋ 80 ሺህ ፣ በጂጂጋ 80 ሺህ እንዲሁም በሀረር 40 ሺህ በአጠቃላይ 200 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና በሲቪክ መስኮች ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ያደርጉ ዘንድ ወደ ስራ ተገብቷል ።
በዛሬው እለትም ፎረም ኦን ሰስተኔብል ችልድረን ኢምፓውርመንት የተቀናጀ የወጣቶች ተግባራት – ከፍታ ፕሮጀክት መክፈቻና ማስተዋወቂያ መድረክ የተካሄደ ሲሆን በዚሁም መድረክ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የሲቪክ ማህበራቶችና ድርጅቶች ዳይሬክቶሬት የሆኑት ወሮ ስሜነሽ አለማየሁ ፎረም ኦን ሰስተኔብል ችልድረን ኢምፓውርመንት በተለያዩ ተቋማት ላይ እየሰራ እንደሚገኝና አሁን ላይ ደግሞ በሶስት ከተሞች ላይ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርገው ” ከፍታ ” የሚለው ፕሮጀክትም ግቡን እንዲመታ የሁሉንም ድጋፍና ርብርብ እንደሚያስፈልግም በእለቱ ገልፀዋል ።
ከፍታ ፕሮጀክት በሀገራችን ላይ የሚገኙ ወጣቶችን በእጅጉ ሊጠቅም የሚችል ፕሮጀክት መሆኑን የፎረም ኦን ሰስተኔብል ችልድረን ኢምፓውርመንት ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሁሴን ሰኢድ ተናግረው መንግስት ለፕሮጀክቱ መሳካት ልዩ ትኩረት ከመስጠት ባለፈ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም ነው አቶ ሁሴን ሰኢድ የተናገሩት ።
በተለይም ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርገው ” የከፍታ ” ፕሮጀክት ከ USAID በተገኘ የገንዘብ ድጋፍና ከሰባት ሀገር በቀል ድርጅቶች ጋር በቅንጅት የሚሰራ ፕሮጀክት ሲሆን ፕሮጀክቱም ወጣቶች የራሳቸውን መብት የሚጠይቁ የሚሞግቱ እንዲሁም በነፃነት መወሰን እንዲችሉ አቅም መገንባት ፣ አዳዲስ የኢኮኖሚ እድሎችን ለወጣቶች መፍጠር ፣ ለወጣቶች ምቹ የሆኑ አገልግሎቶች ተደራሽ እንዲሆኑ በስፋት መስራት መሆኑን ፎረም ኦን ሰስተኔብል ችልድረን ኢምፓውርመንት የቁጥጥርና ክትትል ኦፊሰር የሆኑት አቶ አሸናፊ ደጀኔ ተናግረዋል ።


