4ኛ ዙር የብልጽግና ፓርቲ መምህራን አባላት የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል ።

    “አዲስ ፖለቲካዊ እይታ- አዲስ አገራዊ እምርታ” በሚል መሪ ሀሳብ ትላንት መካሄድ የጀመረው 4ኛ ዙር የአቅም ግንባታ ስልጠና ርዕሶች ማለትም አዲስ ፖለቲካዊ እይታ – አዲስ አገራዊ እምርታ እና ለብልጽግና ጉዟችን የኮሚኒኬሽን ክህሎት እና የሚዲያ ሚና ዙሪያ የብልጽግና ፓርቲ መምህራን እና የቴክኒክና ሙያ አሰልጣኞች አባላት ሊኖራቸው የሚገባ ሚና ዙርያ በስፋት ውይይት ተካሂዶበታል።
    በዛሬው እለትም የብልጽግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅ/ጽ/ቤት ምክትልና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሻኪር አህመድ 3ኛውን ሰነድ: የአስር አመቱ የፓርቲና የመንግስት እቅድ በዝርዝር የቀረበ ሲሆን መምህራን በሀገራዊ እቅዱ በመማር ማስተማር ሂደት የበኩላቸው ድርሻ እንዲወጡና ያገኙትን ግንዛቤ ለሌሎችም በማካፈል እንዲተገበሩ ገልጸዋል።
    4ኛውና የመጨረሻው ሰነድ የፓርቲው የአረደጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደረጀ ጸጋዬ የፓርቲ ተቋማዊ ግንባታ ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን በየት/ቤቶችና ኮሌጆች ጠንካራ መሰረት ያለው ህብረብሄራዊ የሆነ የፓርቲውን ተቋማዊ አሰራር መሰረቶች ያሟላ መዋቅር በመፍጠር አባሉ ያለውን መብትና ግዴታ በማወቅ መንቀሳቀስ ይኖርበታል ብለዋል።
    በማጠቃለያው መምህራን እና የቴክኒክና ሙያ አሰልጣኞች ፓርቲው በአዲስ የፓለቲካ እይታ ማዕቀፍ የሚንቀሳቀስ መሆኑን፣ በሀገራዊ እቅድ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርሙን በአግባቡ በመረዳት የሚዲያ አጠቃቀማቸውን በማሻሻል የፓርቲውን መርህ በማክበር መሰረተ ቢስ ከሆኑ መረጃዎች በመራቅ እንዲሁም የፓርቲውን ራዕይ በመጋራትና የተልዕኮው ባለቤት በመሆን፣ በንቃት በመሳተፍና አስተዋጽኦ በማበርከት እንዲሁም የፓርቲውን ዲስፕሊን በመላበስና በጽናት መቆም እንዳለባቸው መግባባት በመፍጠር የአቅም ግንባታ ስልጠናው ተጠናቅቋል።