የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ በድሬዳዋ ከተማ የተሠሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን አስመረቀ፡፡

    የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ የኢንዱስትሪ መንደር ጤና ጣቢያ፤ በድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል የምህበረሰብ ፋርማሲ/ መድሃኒት መደብር እና የድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል አገልግሎትን ለማዘምን የሚረዳና ከ44 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ የተገዛውን CT Scan/ ሲቲ ስካንና የአገልግሎት መስጫ ክፍልን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር ከድር ጁሃርና የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት አስመርቋል፡፡
    የኢንዱስትሪ መንደር ጤና ጣቢያ ግንባታው በ 2012 ዓ/ም መጨረሻ ተጀምሮ በ20 14 ዓ/ም የተጠናቀቀ ፕሮጀክት ሲሆን ለግንባታውና ለግብዓቶች ማሟያ በጥቅሉ ከ 17 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፡፡
    ይኸው ጤና ጣቢያ ለ 40 ሺ ያክል ሰዎች አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ለ 78 ባለሞያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ቋሚ የሥራ ዕድል ይፈጥራልም ተብሏል፡፡ ሌላው በድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል ቅጥር ጊቢ ውስጥ አገልግሎት እንዲሰጥ በክቡር ከንቲባውና በከፍተኛ የአስተዳደሩ አመራሮች የተመረቀው የማህበረሰብ መድሃኒት መደብር/ ፋርማሲ የመድሃኒት መደርደሪያ/ ሼልፍ በ 623 ሺ ብር እንዲሠራለት የተደረገ ሲሆን መድሃኒት መደብሩ/ ፋርማሲው አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለ 24 ባለሞያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ለማወቅ ተችሏል፡፡
    የድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጥን ከማዘመንም ባሻገር የህብረተሰቡን እንግልት ይቀንሳል ተብሎ የታመነበትና ከ 44 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ግዢው የተፈፀመው CT Scan/ ሲቲ ስካን አገልግሎት መስጠት የሚያስችለው ቤት ግንባታም በ 1.071.547 ብር / ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባለት ሲሆን ይኸው CT Scan/ ሲቲ ስካን አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለድሬዳዋ ነዋሪዎችና ከአጎራባች ክልሎች ለሚመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት ከመስጠትም ባሻገር ለ 6 ባለሞያዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል ሲል የጤና ቢሮ ኮሙኒኬሽን ክፍል ዘግቧል