በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር በሀገራችን ኢትዮጲያ በአራት አመት ውስጥ 20 ቢሊዮን የሚሆኑ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ በሶስት አመት ውስጥ 18 ቢሊዮን የሚሆኑ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን በድሬዳዋ አስተዳደርም በያዝነው አመት ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚሆኑ ችግኞች በከተማና በገጠር ሌላው 200 ሺህ ደግሞ ጅቡቲን ጨምሮ በሌሎች አጎራባች አካባቢዎች ላይ ለመትከልም ታቅዷል ።
በዛሬው እለትም ” አረንጓዴ አሻራችን ለትውልዳችን ” በሚል መሪ ቃል 4 ተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር በድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት አዘጋጅነት በኢትዮጲያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የአዲስ አበባ ጁቡቲ የባቡር መስመር ድሬዳዋ ጣቢያ ላይ ተካሂዷል ።
በዚሁም መርሀ-ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በተቀናጀ የችግኝ ተከላ ስራ የተመዘገቡ ምርጥ ተሞክሮዎችን በአስተዳደሩ የግብርናና ተፋሰስ ልማት በመድገም በተለይም አስተዳደሩ ለበረሀማነትና ተያያዥ የተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭነት አኳያ የተቀናጀ የችግኝ ተከላ ስራ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠቃሚነትና ባለቤትነት በማከናወን በምርትና ምርታማነት ላይ እመርታዊ እድገት ለማረጋገጥ በየደረጃው የምትገኙ አመራሮች ፣ ባለሞያዎች ፣ የልማት አጋሮች እንዲሁም መላው ነዋሪዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉም አቶ ከድር ጁሀር ጠይቀዋል ።
የኢ.ፌ.ድ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብርን ከዛሬ አራት አመት በፊት እንዳስጀመሩና ይህም የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር በየአመቱ ሁሉም ኢትዮጲያዊ በተባበረ ክንድ ችግኞችን እየተከለ እንደሚገኝ የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና በሚኒስቴር ማእረግ የፓርቲው የሲቪክና ፖለቲካ ፓርቲዎች ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት የተከበሩ ዶክተር አለሙ ስሜ ተናግረው በተለይም በአቅም ማነስ ምክንያት በደሳሳ ጎጆ ውስጥ ለሚኖሩ አቅመ ደካማ ለሆኑ እናቶችና አባቶች ቤታቸውን በማደስ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ በመደረግ ላይ እንደሚገኝና ይህም ተግባር ሀገራችን ኢትዮጲያ የመተሳሰብና የመተጋገዝ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑን ዶክተር አለሙ ስሜ ተናግረዋል።
በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር ላይም ተሳታፊ የሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው ለከተማዋም ሆነ ለመኖሪያ አካባቢያቸው አየር ንብረት መለወጥ ከፍተኛ ሚና ያለውን ችግኝ በመትከላቸው መደሰታቸውን ተናግረው የተተከሉትን ችግኞች በቀጣይም እንደሚንከባከቡትም ቃል ገብተዋል ።
በመርሀ-ግብሩ ላይም የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ፣ የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና በሚኒስቴር ማእረግ የፓርቲው የሲቪክና ፖለቲካ ፓርቲዎች ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት የተከበሩ ዶክተር አለሙ ስሜ ፣ የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና በሚኒስቴር ማእረግ የፓርቲው የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት የተከበሩ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ፣ የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና በሚኒስቴር ማእረግ የፓርቲው የስልጠና ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት የተከበሩ አቶ ሞገስ ባልቻ ፣ የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና በሚኒስቴር ማእረግ የፓርቲው የምርጫ ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት የተከበሩ ዛዲግ አብርሀ ፣ የብልፅግና ፓርቲ ማእከላዊ ኮሚቴ አባልና በሚኒስቴር ዲኤታ ማእረግ የፓርቲው የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ሀላፊ የሆኑት የተከበሩ አቶ ካሊድ አሉዋንን ጨምሮ ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ወ\ሮ ፈቲህያ አደን ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ወ\ሮ ከሪማ አሊ ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር የካቢኔ አባላት ፣ የሀይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ አባገዳዎች ፣ ኡጋዞች ፣ ተጋባዥ እንግዶች እንዲሁም መላው የአስተዳደሩ ነዋሪዎች ተገኝተዋል ።


