በድሬዳዋ አስተዳደር ላይ በየቀኑ ሲሚንቶ የሚያመርቱ ሁለት ግዙፍ ፋብሪካዎች ያሉ ሲሆን እነዚህም የናሽናል ሲሚንት አክሲዮን ማህበርና ፓዮኔር ሲሚንቶ ፋብሪካ ናቸው ። እነዚህ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በየቀኑ በርካታ ሲሚንቶዎችን እያመረቱ ቢሆንም ነገር ግን በከተማዋ ላይ በሚፈለገው መጠን የሲሚንቶ አቅርቦት ባለመኖሩ ምክንያት በድሬዳዋ አስተዳደር ላይ ከፍተኛ የሆነ የሲሚንቶ እጥረት እየተስተዋለ ይገኛል ። ይህንንም በማስመልከት የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ፅህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ አሚኑ ጠሃ በዛሬው እለት ለሚዲያ ባለሞያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ሰተዋል።
አሁን ላይ በከተማዋ የተከሰተውን የሲሚንቶ እጥረት ችግር ለመፍታት ይቻል ዘንድ የሚመረተው ሲሚንቶ በተለያዩ የህብረት ስራ ማህበራት ፣ ሸማች ማህበራት እንዲሁም ደግሞ በልማት ድርጅቶች አማካኝነት በቀጥታ ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሚሆንበትን ሁኔታ ለመፍጠር ይቻል ዘንድ መንግስት አዲስ መመሪያ እንዳወጣና ይህም መመሪያ ከሀምሌ 5 ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን አቅጣጫ መቀመጡን አቶ አሚኑ ጠሃ ተናግረዋል።
ከሀምሌ 5 ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ የተቀመጠው መመሪያ በተለይም በአስተዳደሩ ላይ ያሉ የሸማች ህብረት ስራ ማህበራቶች በተለይም ወጣቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ ያበረታታል ፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሲሚንቶን ከፋብሪካ በማውጣት ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ መሆኑንም አቶ አሚኑ ጠሃ ተናግረዋል ።
በድሬዳዋ አስተዳደር ላይ ካሉ ሁሉም ቀበሌዎች ላይ ጠንካራ የሆኑ የህብረት ስራ ማህበራቶችን በመመልመል እነዚህ ማህበራቶችም ሲሚንቶ ከፋብሪካ በማውጣትና መጋዘን ላይ በማስቀመጥ በተቀመጠው ትርፍ ህዳግ መሰረትም ከነገ ወይም ከነገ ወዲያ አንስቶ ሁሉም ማህበራት ሲሚንቶ በማውጣት በየቀበሌው ሲሚንቶ የሚሸጡበትን ሁኔታ መመቻቸቱን አቶ አሙኑ ጠሃ ተናግረዋል ።
ከዚህ ባለፈም በየቀበሌው ያሉ የንግድና ገቢ ማስተባበሪያዎች ይህንን ታሳቢ በማድረግ የገበያ ማረጋጋግት ግብረ ሀይሉን በመጠቀም የሚመጣውን ሲሚንቶ በተቀመጠው በ 5 ፐርሰንት የትርፍ ህዳግ መሰረት ተጠቃሚዎች ሲሚንቶ ማግኘትና መግዛት እንዲችሉ ከማድረግ በዘለለ በጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ሲሚንቶ ለሌላ አላማ እንዳይውል ወይም አየር በአየር እንዳይሸጥ ጥንቃቄ በማድረግ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ አቅጣጫ የተላለፈ በመሆኑ ምክንያት ህብረተሰቡም ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የግንባታ ፍቃድ ያላቸው አካላት ፍቃዳቸውን በማሳየት በንግድ ማስተባበሪያና በንግድ ቢሮ በኩል ሲሚንቶ የሚያገኙበት መንገድ እንደሚፈጠርም ነው ሀላፊው የተናገሩት ።
በድሬዳዋ አስተዳደር ያሉ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በቀን ከሚያመርቱት የሲሚንቶ ምርት ውስጥ 20 ፐርሰንቱን በድሬዳዋ ላይ የመሸጥ ግዴታ እንዳለባቸውና እነዚህንም ሲሚንቶዎች በሸማች ህብረት ስራ ማህበራትና በልማት ድርጅት አማካኝነት በመውሰድ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ የማድረግ ሀላፊነት በመኖሩ ምክንያት ሁሉም የከተማው ነዋሪዎች ይህንን በመከታተል አሁን ላይ በድሬዳዋ አስተዳደር የተከሰተውን የሲሚንቶ እጥረት ችግር መፍታት እንደሚገባቸው አቶ አሚኑ ጠሃ በዛሬው እለት ለሚዲያ አባላት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል ።


