‹‹በጎነት ለጤናችን›› የሚል መሪ ሃሳብ ያለው የነፃ የጤና ምርመራና ህክምና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘመቻ በዛሬው ዕለት የአስተዳደሩ ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሃርና የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ተጠሪ አቶ ዩሱፍ ኢብራሂም እንዲሁም ሌሎች የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል፡፡
በመክፈቻ መረሃ-ግብሩ ተገኝተው የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ነፃ የጤና ምርመራና ህክምና ዘመቻውን በይፋ ያስጀመሩት የአስተዳደሩ ከንቲባ ክቡር አቶ ከዲር ጁሃር ይህንን ‹‹በጎነት ለጤናችን›› በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀውን የበጎ አድራጎት ዘመቻን ለመደገፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የግልና የመንግስት ጤና ተቋማትን አመስግነው በተለይ በዘመቻው ላይ ለመሳተፍና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመስጠት የጤና ባለሞያዎችንና የተለያዩ የህክምና ግብዓቶችን ይዘው በአገልግሎት መስጫ ሥፍራው ላይ የተገኙትን ዳዊት የማሪያም ወርቅ ፋውንዴሽንን በአስተዳደሩ ስም ከልብ አመሰግናለሁ ብለዋል፡፡
ክቡር ከንቲባው ጨምረውም የአስተዳደራችን ነዋሪ ጤናማነቱን ለማረጋገጥና ጤናውን መጠበቅና መከታተል እንዲቻለው በተዘጋጁት የዘመቻው አገልግሎት መስጫ ቦታዎች በመገኘት በነፃ የጤና ምርመራ በማድረግ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ በበኩላቸው የጤና ሥራ በባህሪው የበጎነት ሥራ ሲሆን ይህንኑ ተከትሎ ‹‹በጎነት ለጤናችን›› በሚል መሪ ሀሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ነፃ የህክምና አገልፍሎት በድሬዳዋ አስተዳደር ለ አምስት ሺ ሰዎች ምርመራና ህክምና እነዲሁም የጤና ትምህርቶችን ለመስጠት ዝግጅታችንን አጠናቀናል ብለዋል፡፡
ይኸው ዘመቻ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር የህክምና ቁሳቁስ ድጋፎችን በማሰባሰብ እና የጤና ባለሞያዎችን በመመደብ ለአንድ ሳምንት ዋና ዋና ለሚባሉ ህመሞች ምርመራ የምናደርግ ሲሆን ተመርምረው የጤና ችግር ለተገኘባቸውና ከፍለው መድሃኒት መግዛት ለማይችሉ እንዲሁም ተጨማሪ ህክምና ለሚያስፈልጋቸው በጤና ተቋማቶቻችን ነፃ ህክምና እና መድሃኒቶችንም የምንሰጥ ሲሆን የጤና ምርመራ አገልግሎቶቹን በኮኔል፣ በለገሃር/ኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር እና በሳቢያን ሰኢዶ ማደያ በተዘጋጁት የምርመራ ማዕከላት በመገኘት መመርመር እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
ኃላፊዋ አይይዘውም በዚሁ የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ለተሳተፉና ድጋፍ ላደረጉ የመንግስትና የግል ጤና ተቋማት በተለይም ለዳዊት የማርያም ወርቅ ፋውንዴሽን እና ለቀይ መስቀል ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ከዚሁ ዘመቻ ጋር ተያይዞ የጤና ቢሮ ሠራተኞችና በቢሮው ስር የሚገኙ ጤና ተቋማት ሠራተኞች ገንዘብና አልባሳትን በማሰባሰብ እንዲሁም መአድ የማጋራት ተግባርን ከማከናወንም ባሻገር የአንድ አቅመ ደካማ ነዋሪን ቤት የማደስና መሰረታዊ የቤት ቁሳቁሶችን የማሟላት ሥራም ይከናወናል ብለዋልሲል የዘገበዉ ጤና ቢሮ ኮሙኒኬሽን ክፍል ነዉ


