በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ ወጣቶች ከአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያዩ ።

    ” የአስተዳደራችንን ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ የድሬዳዋን ብልፅግና እውን ለማድረግ የወጣቱ ሚና ከፍተኛ ነው ” በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬው እለት በ ቢ ካፒታል ሆቴል መሰብሰቢያ አዳራሽ በድሬዳዋ አስተዳደር በከተማም ሆነ በገጠር ከሚገኙ ወጣቶች ጋር የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል ።
    በዚሁም ውይይት ላይ ተሳታፊ የሆኑ የአስተዳደሩ ወጣቶች የተለያዩ ሀሳብ አስትያየቶችን ያነሱ ሲሆን በተለይም በከተማው ላይ ያሉ ወጣት ማእከላት ለወጣቶች ተገቢውን አገልግሎት ሊሰጡ በሚችሉበት መልኩ ሊሆኑ እንደሚገባ ፣ የስራ እድል ፈጠራ ላይ በቀጣይ በትኩረት እንዲሰራ ፣ ወጣቱንና የከተማውን አመራሮች በይበልጥ ሊያቀራርቡ የሚችሉ ስራዎች እንዲሰሩ ፣ አሁን ላይ በከተማዋ የተለያዩ የልማት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙና እነዚህም የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ነው ወጣቶቹ ያነሱት ።
    ከዚህ ባለፈም በአስተዳደሩ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባቸውና ከምንም በላይ ግን ለድሬዳዋ እድገትና ብልፅግና በጋራ በመሆን መስራት እንደሚገባም ነው ወጣቶቹ በውይይቱ ላይ ያነሱት ።
    በድሬዳዋ አስተዳደር በገጠርና በከተማ የውሀ ፣ የመንገድ ፣ የትምህርት ፣ የጤና እንዲሁም ሌሎች በርካታ የልማት ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ተናግረው በአስተዳደሩ ላይም የኩላሊት እጥበት ማሽን በአንድ ባለሀብት አማካኝነት ግዢ ከመደረጉም ባለፈ የናሽናል ሲሚንት አክሲዮን ማህበር ለኩላሊት እጥበት ማሽን የሚሰጥበት ማእከል የቤት ግንበታ እንዳደረገና በቅርብ ቀናት ውስጥም ተመርቆ ወደ አገልግሎት እንደሚገባም ክቡር ከንቲባው በእለቱ ተናግረዋል ።
    ክቡር ከንቲባው አክለውም በያዝነው አመት በከተማዋ ላይ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ አምስት ሆቴሎችን ግንባታ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ ከመሆኑም ባለፈ በምድር ባቡር ቅጥር ግቢ ውስጥ ላይ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ለህዝብ መዝናኛነት ክፍት የማድረጉ ስራ እንደሚሰራና የከተማው አመራሮችም ለወጣቶች ብሎም ለከተማው ነዋሪዎች ቀን ከለሊት ለመስራትና ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረው ከምንም በላይ ግን የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ በዘላቂነት የማረጋገጥ ስራዎች ላይ በጋራ በመሆን ከመስራት ባለፈ የከተማዋን እድገትና ብልፅግና እውን ለማድረግም በጋራ በመሆን መስራት እንደሚገባም ነው ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሀር የተናገሩት ።
    በውይይቱ ማጠቃለያ ላይም በድሬዳዋ አስተዳደር በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ የሆነ ለውጥ እንዲመጣ እንዲሁም ለከተማው ወጣቶች ላበረከቱት ከፍተኛ የሆነ አስተዋፆ ለድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ እንዲሁም የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን የተዘጋጀ የእውቅና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል ።
    በአለማየሁ አበበ ።
    ፎቶ :- በይድነቃቸው አብርሃም ።