ያገለገሉ የፕላስቲክ ኮዳዎችን መልሶ ጥቅም ላይ የሚያውል ግዙፍ ፋብሪካ በድሬዳዋ አስተዳደር ስራውን በይፋ ጀመረ ።

    በ 10 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ከ 400 ሚሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ የተገነባውና ያገለገሉ የፕላስቲክ ኮዳዎችን መልሶ ጥቅም ላይ የሚያውለው የመንገሻ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ( MIG ) ፋብሪካን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀርን ጨምሮ ከፍተኛ የአስተዳደሩ አመራሮች በተገኙበት ተመርቋል ።
    በዚሁም የምርቃት መርሀ-ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር የመንገሻ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ( MIG ) ፋብሪካ እውን እንዲሆን አስተዳደሩ ለፋብሪካው የሚሆን በቂ መሬት ከማዘጋጀት አንስቶ በተለያዩ ጊዜያቶች ፋብሪካውን በቅርበት ይከታተሉት እንደነበር ተናግረው አሁን ላይም በአስተዳደሩ ላይ በተለያዩ መስኮች ለውጦች እየመጡ እንደመሆናቸው መጠን እነዚህም ለውጦች ተጠናክረው ይቀጥሉ ዘንድ በጋራ መስራት እንደሚገባም ነው ክቡር ከንቲባው በእለቱ ያስታወቁት ።
    የመንገሻ ኢንቨስትመንት ግሩፕን ስኬታማ ለማድረግ በርካታ ውጣ ውረዶች ቢኖሩም ነገር ግን ፋብሪካው በሀገራችን ላይ ካሉ ሌሎች ፋብሪካዎች ሊወዳደር በሚችል መልኩ አስፈላጊ የሆኑ ማሽኖችንና ሌሎች ማቴሪያሎችን በሟሟላት ለምርቃ ቀን መብቃቱን የመንገሻ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ( MIG ) ባለቤትና ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ አበበ መንገሻ ተናግረው ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባም ከ 150 በላይ የሚሆኑ ሰራተኞችን እንደሚቀጥርና በተዘዋዋሪ ደግሞ ከ 10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ከፍተኛ የሆነ የስራ እድል መፍጠር እንደሚችልም አቶ አበበ መንገሻ ተናግረዋል ።
    የመንገሻ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ( MIG ) ፋብሪካ ለድሬዳዋ አስተዳደር ፅዳትና ውበት እንዲሁም ለከተማዋ ነዋሪዎች ከፍተኛ የሆነ የስራ እድልን የሚፈጥር በመሆኑ ፋብሪካው ለዛሬው የምርቃት ቀን በመብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ የድሬዳዋ አስተዳደር የስራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሮቤል ጌታቸው ተናግረዋል ።
    የመንገሻ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ( MIG ) ፋብሪካ የምርቃት ስነ-ስርአት ላይም የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀርን ጨምሮ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ ፣ ከፍተኛ የአስተዳደሩ አመራሮች ፣ የመንገሻ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ( MIG ) ባለቤትና ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ አበበ መንገሻ ቤተሰቦችና ጓደኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ።
    በአለማየሁ አበበ ።
    ፎቶ :- በይድነቃቸው አብርሃም ።