43ኛ ዙር የጽዳት ዘመቻ አገልግሎት በአስተዳደሩ በቀበሌ 07 ጫት ተራ አካባቢ ተካሄደ፡፡

    በዛሬው እለት 43ኛ ዙር የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች የፌ.ደ.ራ.ል የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር፣ ዲያስፖራዎች፣ የቀበሌ 07 አስተዳደር አመራሮች ፣ የጽዳት አገልግሎት የሚሰጡ አካላት እና በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት የጽዳት ዘመቻ ተካሂዷል።
    በጽዳት ዘመቻ ወቅት የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ክቡር ሀርቢ ቡሁ እንደተናገሩት አዲሱ መስተዳደር ከመጣ ጀምሮ በየሳምንቱ በሁለት ምድብ በ9ኙም ቀበሌዎች ተከታታይነት ያለው ሰፊ የጽዳት ዘመቻ በማከናወን ላይ መሆናቸውን እና ዘመቻውን ህዝባዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
    የከተማዋን ራዕይ በማሳካት በኩል ከተቀመጡት ግቦችም ፤ ድሬደዋን ውብ ጽዱ ፣ለንግድ ፣ለኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ምቹ ማድረግ የሚለውን ተልእኮ ለማሳካት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
    በመሆኑም የጽዳት ዘመቻውን ህዝባዊ ለማድረግ በየቀበሌው የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን እና ግለሰቦች እስከ 20 ሜትር ደርጅቶች እስከ 50 ሜትር ርቀት ድረስ እንዲያጸዱ መግባባት ላይ የተደረሰ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
    የድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍም በበኩላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ በአስተዳደሩ ቆሻሻ የማመንጨት መጠን ጨምሯል ይህም የሚያሳየን የከተማው መነቃቃት የሚያመላክት በመሆኑ ከተጋገዝን ከተማችንን ውብ እና ጽዱ ማድረግ ይቻላል ብለው አክለውም አመራሩ ሳይሰላቸ ህዝቡን በንቃት በማሳተፍ ውጤታማ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
    የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚንስተር ድኤታ አቶ ወንድሙ ሴታ የድሬደዋ ከተማ ከዚህ በፊት ያላትን ጽዱ እና ማራኪ እይታ ያለት ተመራጭ ከተማ መሆኗን አውስተው ያንን ለመመለስም እየተሰሩ ያሉትን ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
    በተለይም በአሁኑ ሰዓት ለከተማዋ የመጣውን እድል በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል ፤ ተረፈ ምርቶች በስርዓት በመያዝ ቆሻሻን ማጽዳት ብቻ ሳይሆን አለመጣልና በትክክለኛ ቦታ ማስቀመጥ ነው መፍትሄው ያሉ ሲሆን በአስተዳደሩ በተጀመረው የጽዳት ዘመቻ የአመራር ቁርጠኝነት አጠናክሮ በማስቀጠል በጽዳት የተጀመረውን እንቅስቃሴ በማሳካት ወደ አረንጋዴ ልማት ስራዎች መግባት ስለሚያስፈልግ ሚንስትር መስሪያ ቤቱም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋልም ነው ያሉት ሚንስትሩ ።