የድሬዳዋ የቀድሞ ከንቲባ ክቡር አልፍሬድ ሻፊ ቤተሰቦች ለአስተዳደሩ ምስጋናቸውን አቀረቡ።

ቤተሰቡ ከምስጋናው በተጨማሪም ለድሬዳዋ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር የግማሽ ሚሊየን ብር የገንዘብ ስጦታ በግል አበርክቷል።
በድሬዳዋ ዘመናዊ የከተማነት ስልጣኔ ታሪክ ውስጥ፤ ጉልህ ሚና ከነበራቸው ተጠቃሽ አመራሮች መካከል፤ የቀድሞው ክቡር ከንቲባ አልፍሬድ ሻፊ ዋነኛው ናቸው።
ከንቲባው በመሪነት ዘመናቸው ለድሬዳዋ ያበረከቱት የልማት ትሩፋትና ህዝብን የማስተዳደር መልካም ስማቸው ለትውልድ በክብር እንዲተላለፍ፤ እርሳቸው ያስገነቡት ጥንታዊው የኮኔል ድልድይ “የአልፍሬድ ሻፊ ድልድይ” ተብሎ እንዲጠራ ከወራት በፊት አስተዳደሩ መወሰኑ ይታወሳል።
በውጭ አገር የሚኖሩ የአልፍሬድ ሻፊ ልጆችና መላው ቤተሰቦቻቸው ተሰብስበው በመምጣት፤ አስተዳደሩ ለአባታቸው በሰጠው ክብር የተሰማቸውን ልዩ ደስታ እና ምስጋና፤ የድሬዳዋ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በተገኙበት መድረክ ላይ ገልፀዋል።
ከአስርት ዓመታት በፊት አባታቸው ያስተዳደራትን ከተማ በማየታቸው መደሰታቸውን እና በድሬዳዋ እየታየ በሚገኘው ሁለንተናዊ ፈጣን እድገት እንደተደነቁ የገለፁት የአልፍሬድ ሻፊ ቤተሰቦች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳደረባቸው አስታውቀዋል።
ከንቲባ አልፍሬድ ሻፊ ቢሮ መቀመጥ እንደማይወዱ፤ ይልቁንም ወደ ማህበረሰቡ በመዝለቅ ለመልካም አስተዳደር ችግሮች ፈጣን መፍትሄ ይሰጡ እንደነበር በታሪክ መስማታቸውን የተናገሩት በአስተዳደሩ ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ፤ ከዚህ የመሪነት ተግባራቸው እኛ ተምረናል እናንተ ደግሞ ልትኮሩ ይገባል ብለዋል።
ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሀር ለአስተዳደሩ መልካም ድርጊት እውቅና በመስጠት ባህር አቋርጠው ለመጡት ለቀድሞ ከንቲባ አልፍሬድ ሻፊ ቤተሰቦች ያላቸውን ክብር የገለፁ ሲሆን፤ አባታቸው ለድሬዳዋ ህዝብ ያበረከተውን አስተዋጽኦ፤ ልጆቻቸው በአስተዳደሩ ኢንቨስት በማድረግና በበጎ ስራዎች በመሳተፍ እንዲደግሙት ጠይቀዋል።
ከአልፍሬድ ሻፊ ቤተሰብ ለሚፈልጉት የልማት ስራ እንዲያውሉት በግል የግማሽ ሚሊየን ብር ስጦታ የተበረከተላቸው ከንቲባ ከድር ጁሀር፤ በስጦታ ያገኙትን ገንዘብ በአስተዳደሩ ለሚገኙ እና በኩላሊት ህመም ለሚሰቃዩ ወገኖቻቸው ለመስጠት ቃል የገቡ ሲሆን፤ ለስጦታው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በመጨረሻም ከንቲባ ከድር ጁሀር በማጠቃለያ ንግግራቸው፤ “ከቀደሙ መሪዎች የአመራር ጥበብና የስራ ልምድ በመማር፤ ሙሉ አቅማችንን ለድሬዳዋ እድገት እያዋልን የተሰጠንን ህዝባዊ ኃላፊነት በመወጣት፤ የብልጽግና ጉዟችንን እንቀጥላለን” ሲሉ አቋማቸውን ገልፀዋል።
የድሬዳዋ ከንቲባ ጽ/ቤት