የድሬደዋ አሰተዳደር ምክር ቤት የግብርና ተፈጥሮ ሀብትና አከባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በከተማ ግብርና ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ጎበኘ።

የድሬደዋ አሰተዳደር ምክር ቤት የግብርና፣ ተፈጥሮ ሀብትና አከባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከታህሳስ 24/2015 ዓ.ም ጀምሮ በከተማና በገጠር በግብርናው ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን እየጎበኘ ሲገኝ በዛሬ ውሎውም በአካባቢ ልማት ኤጀንሲና በተደራጁ ወጣቶች የተሰሩ ስራዎችን ጎብኝቷል።
በዚህም በከንቲባ ጽ/ቤት ጊቢ ውስጥ የሚገኙ ችግኞችን፣ በጎሮ ት/ቤት የሚገኙትን የተለያዩ የደረሱ አትክልቶችን እንዲሁም በገንደ ተስፋ አካባቢ በመገኘት በከተማ ግብርና ላይ እየተሰሩ ያሉትን ስራዎች ተመልክተዋል።
ቋሚ ኮሚቴው በከንቲባ ጽ/ቤት ጊቢ ውስጥ ሁለት ቦታ ላይ በጎማና በፒፒሲ የተተከሉ ችግኞችን ጎብኝቷል። ይህም ለጊቢው ውበት እንደሚለግስ የተገለፀ ሲሆን ችግኞቹ በቂ የሆነ አየር፣ ውሃና የፀሀይ ብርሀን ማግኘት ስላለባቸው በቀጣይ በምቹ ቦታ ላይ መተከል እንደሚገባቸውም አቅጣጫን አስቀምጠዋል።
በቀጣይ ቋሚ ኮሚቴው በጎሮ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የሚገኙትን የተለያዩ አትክልቶችን የጎበኘ ሲሆን በዚህም ሰላጣ፣ ጥቅል ጎመን፣ ቃሪያ፣ ቲማንቲምንና እና ሌሎችንም የደረሱ አታክልቶችን ተዘዋውረው አይተዋል። ይህንን የአካባቢው ልማት ኤጀንሲ የጀመረውን የጓሮ አትክልትም እንደ አስተዳደር በሁሉም የግልና የመንግስት ተቋማት ላይ በማስፋፋት ነዋሪውን ከኑሮ ውድነት ማውጣት እንደሚቻልም የድሬደዋ አሰተዳደር ምክር ቤት የግብርና ተፈጥሮ ሀብትና አከባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት የተከበሩ አቶ አህመድ አብዶ ተናግረዋል።
በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው በገንደ ተስፋ አካባቢ የከተማ ግብርናን ተደራጅተው የሚሰሩ ወጣቶችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም የብርትኳን፣ የማሽላና የጫት ግንዶችን ተመልክተዋል። ወጣቶች የማይጠቅሟቸው ነገሮች ላይ ጊዜአቸውን ከሚያጠፉ ይልቅ ወደዚህ ልማታዊ ስራ መግባታቸው አስፈላጊ በመሆኑ ወጣቶቹ ሊደገፉ እንደሚገባም ተገልጿል። አካባቢው ላይ የውሃ እጥረት በመኖሩ ወጣቶቹ የውሃ ጉድጓድ በባህላዊ መንገድ ቆፍረው ያወጡ ሲሆን ይህንን ዘመናዊ ለማድረግ የሚመለከተው አካል ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው አቶ አህመድ አሳስበዋል።
ባጠቃላይ አሁን ላይ በዚህ በከተማ ግብርና ላይ ጥሩ ጅምሮች እንዳሉና ለቀጣይም ተስፋ ሰጪ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም አቶ አህመድ አብዶ ገልፀዋል።