ኢትዮጵያ በቀጠናው በኢነርጂ እና አቪዬሽን ዘርፍ ትብብር ብሎም ትስስር እንዲኖር አበክራ እየሰራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ሀገሪቱ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ዕምቅ አቅም እንዳላት ገልፀዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኬኒያ እና ታንዛኒያ ጉብኝት በአቪዬሽን እና ኢነርጂ ዘርፍ አካባቢያዊ ትስስር እንዲኖር ለማድረግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
አምባሳደር መለስ በመግለጫቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከሁለቱ ሀገራት ጋር ጠንካራ እና ረጅም ዓመት ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ትስስር አላት።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ውጤታማ መሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ፤ በኢነርጂ እና አቪዬሽን ዘርፎች ኢትዮጵያ የምታካሂደው ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ውጤታማ መሆኑ የታየበት ነው ብለዋል።


