ከዛሬ ሁለት ወር በፊት በክብር አርቲስት ዶክተር አሊ ቢራ ስም በተሰየመው የገንደ ገበታ አንደኛ እና መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን ለመገንባት ይቻል ዘንድ የመሰረት ድንጋይ መቀመጡ ይታወሳል ። በትምህርት ቤቱ ላይም የመሰረተ ድንጋይ ከተቀመጠበት እለት አንስቶም ግንባታው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን በዛሬው እለትም የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሀር ፣ በብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ እንዲሁም የመማሪያ ክፍሎቹን እያስገነባ ያለው ኢንጂነር ነገራ ዱጉማ ፣ ነጃት ፈድሉ እንዲሁም ሀጂ መሀመድ ኡመር በጋራ በመሆን ግንባታውን ጎብኝተዋል።
በክብር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ስም በተሰየመው የገንደ ገበታ አንደኛና መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ እየተገነቡ ያሉት ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለተማሪዎች አገልግሎት እንደሚሰጡ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሀር ተናግረው በተለይም ትምህርት ቤቱ ከ 21 ቋንቋ በላይ ለማስተማር ይችል ዘንድ እየተሰራ ከመሆኑም በላይ ተማሪዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ትምህርታቸውን እንዲማሩ እንደሚደረግም ነው ክቡር ከንቲባው በእለቱ የተናገሩት ።
የክብር አርቲስት ዶክተር አሊ ቢራ አንደኛ አመት በድሬዳዋ አስተዳደር ላይ በሚከበርበት ወቅት በክብር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ስም በተሰየመው ገንደ ገበታ አንደኛና መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ በመገኘት ትምህርት ቤቱን መመልከቱን የኤንዲ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለቤት እና ስራ አስኪያጅ የሆነው ኢንጂነር ነገራ ዱጉማ ተናግረው በዚህም ትምህርት ቤት ላይ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን ለመገንባት ቃል በመግባት እና ግንባታውን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማስጀመር የመማሪያ ክፍሎቹ አሁን ላይ ከ 90 ፐርሰንት በላይ ተጠናቀው የፊኒሺንግ ስራዎች ብቻ እንደሚቀሩት ነው ኢንጂነር ነገራ ዱጉማ የተናገሩት ።
ኢንጂነር ነገራ ዱጉማ አክለውም በአሜሪካን ሀገር የሚኖረው የቅርብ ጓደኛው የሆነው ለሊሳ ሂካ በውጪ ሀገር ከሚኖሩ ጓደኞቹ ጋር በጋራ በመሆን በትምህርት ቤቱ ውስጥ ዘመናዊ ሳተላይት እና ፕላዝማ ለማስገባት ቃል እንደገባና ይህም በቀጣይ ቀናት በትምህርት ቤቱ ላይ ተግባራዊ በማድረግ ተማሪዎቹ በዘማናዊ ሳተላይት እና ፕላዝማ በመታገዝ ትምህርታቸውን እንደሚማሩም ነው ኢንጂነር ነገራ ዱጉማ የተናገሩት ።


