በድሬዳዋ አስተዳደር አሰሊሶ ወረዳ “የተቀነጀ ተፋሰስ ለዘላቂ አረንጓዴ ልማት” በሚል መሪ ቃል ለ30 ቀናት ስካሄድ የነበረው የበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት ስራ ዛሬ ተጠናቋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጆሀር በመዝጊያ መርሀ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት የበለጸገ አካባቢ እና ኢኮኖሚ በመገንባት ለትውልድ ምንዳ ለማስተላለፍ የላቀ ሚና ያለው መሆኑን ጠቅሰው የዘንድሮው የ30 ቀናት የተፋስ ስራ በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት፤ በላቀ አደረጃጀት እና ቅንጅታዊ አሰራር መሰራቱንና እንደ አስተዳደርም የአፈርና ውሀ ጥበቃ እንዲሁም በገጠር የተለያዩ ማህበራዊ ዘርፎች ከተከናወኑት ተግባራት እጅግ ከፍተኛ ለውጥ እና መልካም ተሞክሮዎች ከተመዘገበባቸው የልማት ስራዎች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ክቡር ከንቲባው አክለውም የተቀናጀ የበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ለአስተዳደራችን ምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ከግምት በማስገባት በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመፍጠር፣ የአርሶና አርብቶ አደሩን የኢኮኖሚ ደረጃን በዘመናዊ ጥምር ግብርና በመምራት የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥ፣ ሁሉም ሰው መረባረብ እነዳለበት በመግለፅ የሀሳሊሶ ክላስተር በተለይም ሪጌ መንደር ማህበረሰብ የዘንድሮውን የተፋሰሱ ስራ ሌት ተቀን በመስራት ከእቅድ በላይ በማሳካቱ የእነኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
በቀጣዩም የክረምት ልማት ስራ ሁላችንም በየደረጃው ካሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት በመስራት ለመጪው ትውልድ የበለፀገች አገር ማስተላለፍ አለብን ሲሉም ክቡር ከንቲባ ጨምረው ገልፀዋል ፡፡
በፊደራል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስተዳደሩ ተወካይ አቶ አብዱልጀዋድ መሀመድ በመርሀ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር አስተዳደሩ የህዝባችንን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በቁርጠኝነት እየፈታ ያለ መሆኑንና ያልተመለሱ የልማት ችግሮችም በሂደት እንደሚመለሱ ጠቅሰው ሕዝቡም በበጋ ወራት የተፋሰስ ስራ ላይ ባሳዩት ከፍተኛ የስራ ተነሳሽነት በኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዘርፍ በማስቀጠል ባጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት እነደምቻል አስተያየታቸውን ሰተዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር የግብርና ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን ዐብደል በበኩላቸው በዘንድሮው የበጋ ወራት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ 4 ሺህ 662 ሄክታር መሬት የሚሸፍን የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን በማከናወን የመሬት መራቆት ችግርን በ 3 ነጥብ 1 በመቶ ለመቀነስ እና በጎርፍ ሊወሰድ የሚችለውን 40 ሺህ 800 ቶን ለም አፈር በማዳን ከተቀመጠው ግብ 84 በመቶ ለማሳካት እንደተቻለ ገልፀዋል ፡፡
በመርኃ ግብሩ ላይ በርካታ የአስተዳደሩና የወረዳው የስራ ኃላፊዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች የተገኙ ሲሆን በተፋሰሱ ስራ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱና ጥሩ ውጤት ላስመዘገቡ ቀበሌዎች ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷል።


