የድሬዳዋ አስተዳደር የከንቲባ ጽ/ቤት አመራሮች እና ፈፃሚ ባለሙያዋች “ሴቶችን እናብቃ ልማትና ሰላምን እናረጋግጥ!” በሚል መሪ ሀሳብ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን አክብረዋል።
ዕለቱን አስመልክቶ የከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁን ባስተላለፉት መልዕክት÷ የሴቶችን መብትና የፆታ እኩልነት በማረጋገጥ በሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የልማት ተሳትፎዎች ላይ ያላቸውን ድርሻ ለማሳደግ በሁሉም ዘርፍ እየሠራን ነው ብለዋል።
የጽ/ቤቱ ኃላፊ ከዚህም ጋር በማያያዝ ቀኑንን ከመዘከር ባለፈ ለአገር ግንባታ የሴቶች ሚና የጎላ በመሆኑ በተሰማራንበት የስራ መስክ ሁላችንም በጋራ መቆም ይኖርብናል ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ ክብርት ሰአዳ አዋሌ በበኩላቸው በተሰማራንበት የስራ መስክ ውጤታማ አመራር እና ባለሙያዋች በመሆን የአገልግሎት አሰጣጣችን ብቃት እና ጥራት ያለው በማድረግ የተጣለብንን ኃላፊነት መወጣት አለብን ብለዋል።
የጽ/ቤቱ ምክትል ኃላፊ አክለውም አቅም በፈቀደ መልኩ አረጋዊያንን እና ወላጅ አልባ ህፃናትን የመደገፍ ስራዋችን መስራት አለብን ብለዋል።
የከንቲባ ጽ/ቤት የስርአተ ፆታ ፎካል ወ/ሮ መሀሌት ንጋቱ ባስተላለፉት መልዕክት በተቋማቸው ሴቶችን ከማብቃት አንፃር የትምህርት እድል፣የደረጃ እድገት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና በተለያዩ ማህበራዊ ዘርፎች በግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጉን ገልፀዋል።
በመድረኩም አለም አቀፍ የሴቶች ቀን አስመልክቶ ማብራሪያ ተሰቷል በማስከተልም ቀኑን በማስመልከት ጥያቄዋች ቀርበው ውድድሩን ላሸነፉ ተወዳዳሪዋች ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።


