የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ በክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ የተመራ የሱፐርቪዥን ቡድን በድሬዳዋ አስተዳደር ሲያካሂድ የቆየውን ድጋፋዊ ሱፐርቪዥን አጠናቆ ግብረመልስ ሰጥቷል፡፡
ልኡክ ቡድኑ ለአንድ ሳምንት ባካሄደው ድጋፋዊ የመስክ ምልከታና ክትትል ዙሪያም የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ክቡር ሀርቢ ቡህ በተገኙበት አጠቃላይ ግብረ መልስ ሰቶ ውይይት ተደርጓል።
በዚህም ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡድኑ ላደረገው ድጋፋዊ ጉብኝት አመስግነው፤ እንደነዚህ አይነት ጉብኝቶች በአስተዳድሩ የሚስተዋሉና በፌደራል ደረጃ መቀረፍ የሚገባቸውን ችግሮች ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳላቸው ገልፀዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ስራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው ክፍተት የታየባቸው ስራዎች ላይ እቅድ ተይዞ ለማስተካከል እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ በበኩላቸው በቆይታቸው ኢንተርፕራይዞችን፣ ወረዳዎችን፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን፣ ኢንደስትሪዎችን እንዲሁም የአሰሪና ሰራተኞች ግንኙነትን እንደተመለከቱ የገለፁ ሲሆን፤ ድሬዳዋ ላይ የተመለከቱት ስራም የሚበረታታና ወደ ሌሎች አካባቢዎች በተሞክሮነት ሊወሰድ የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል።
በክህሎት ልማቱ በኩል በርካታ ስራዎች እንደተሰሩ ያነሱት አቶ ዳንኤል የወጣቶችን ፍላጎትና ገበያውን መሰረት ያደረገ ስልጠና እየተሰጠ እንዳለ በመጥቀስ በዚሁ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በተያያዘም የሪፎርም ስራ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ እንደሚገኝ፣ ወጣቶች እንዲደራጁ ድጋፍ እየተደረገ እንደሆነና፤ በስራ እድል ፈጠራም በርካታ ወጣቶች ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኝ እንዲሁም ወጣቶችን ወደ ኢንተርፕራይዝ የማደራጀት ስራ እየተከናወነ እንደሆነና የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነትን በተመለከተ አበረታች ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ሚኒስተር ደኤታው ገልፀዋል።
በአጠቃላይም ድሬደዋ ላይ እየተሰሩ ያሉት ስራዎች አበረታች መሆናቸውን አቶ ዳንኤል አንስተው ጅምር ስራዎችንም በማጠናከሩ ረገድ ሚኒስተር መስሪያ ቤቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።


