በኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደር ድሬዳዋ ቅርንጫፍና በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ትብብር ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ህጻናት ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሒዷል ፡፡
ወላጆቻቸውን በተለያዩ ምክንያቶች ያጡ ህጻናትን በመንደር በማሰባሰብ ሁለንተናዊ የእድገት መሰረታቸው ተጠብቆ እንዲያጉ እየሰራ የሚገኘው ኤስ ኦ ኤስ ( SOS) ህጻናት ወደ ጎዳና እንዳይወጡ የቤተሰብ ማጠናከሪያ ፕሮጄክት ቀርጾ እየተገበረ መሆኑን የሐረር ኤስ ኦ ኤስ ህጻናት መንደር ዋና ዳይሬክተር አቶ አንዷለም ጌታቸው ገልጸው ፤ ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ህጻናትን ለመደገፍም በድሬዳዋ አስተዳደር ላለፉት ሁለት ዓመታት እየሰራን ነው ብለዋል ፡፡
ህጻናትን የሚመለከቱ የህግ ማእቀፎች ህጻናት ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ የሚያደርጉ ገፊ ምክንያቶች ፣ በጎዳና ላይ ህጻናቱን የሚደርሱባቸው ችግሮችን የሚያሳዩ ሁለት የውይይት መነሻ ጽሁፎች በድሬዳዋ ኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ አለምሰገድ ደጀኔና በኤስ ኦ ኤስ ህጻናት የድሬዳዋ ፕሮጄክት አስተባባሪ አቶ ሚካኤል ስንታየሁ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል ፡፡
ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደሩ ህጻናት ስንል እድሜያቸው እስከ አስራ ስምንት ዓመት ድረስ ያሉት ላይ ብቻ እንዲተኮር ስለሚያደርግ በተቀራራቢ የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉትን ያላካተተና አግላይ ትግበራ እንዳይሆን ታሳቢ መደረግ አለበት ፣ ዕነዚህን ወገኖች ለመደገፍ የሚተገቡ ፕሮጄክቶች ለችግሩ መፍትሔ ከመሆን ይልቅ ሳቢ ምክንያት እንዳይሆኑ በጥንቃቄ ሊጤኑ ይገባል ፣ ህጻናቱ ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ካደረጉ በኋላ የሚተገቡ ፕሮጄክቶች ችግሩንሙሉ ለሙሉ መቅረፍ ስለማያስችሉ ሳቢና ገፊ ምክንያቶችን በጥናት ለይቶ እዛ ላይ ርብርብ ቢደረግ የተሸለ ይሆናል የሚሉ ሃሳቦች ከውይይቱ ተሳታፊዎች ተሰንዝረዋል ፡፡
ህጻናት የሚሰነዘሩባቸውን ጥቃቶች ለመከላከል አእምሯዊና አካላዊ ብቃት የሌላቸው መሆናቸውና ውሎና አዳራቸው ደግሞ ጎዳና ሲሆን የሚደርስባቸውን ጉዳት የከፋ ስለሚያደርገው ህጉ ልዩ ከለላ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ የተወሳ ሲሆን በተለይም እነዚህ ህጻናት የተለያዩ ችግሮች ሲያጋጥሟቸውም አስፈላጊ ግልጋሎችን እንዳያገኙ የምዝገባና ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ የሌላቸው መሆናቸውም ችግራቸውን ድርብርብ እያደረገው ይገኛል ተብሏል ፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ባደረጉ ህጻናት ላይ አራት የተለያዩ ጥናቶችን በቅርብ ጊዜያት ማከናወኑን እና የጥናት ግኝቶቹን መሰረት አድርገው ፕሮጄክቶችን መተግበር የሚሹአካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚችሉ ተጠቁሟል ፡፡
ካለው የችግሩ ስፋት አንጻርና ከሚያስፈልገው በጀት አኳያ የተሰሩ ስራዎች ችግሩን እንዴት መቅረፍ ይቻላል የሚለውን ከማመላከት የሚያልፉ ስለማይሆን ዘላቂ መፍትሔ ከማጣት አንጻር ሁሉን አቀፍ ትብብርና ትኩረት ያስፈልጋል ለዚህም የባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ያሉት በድሬዳዋ አስተዳደር ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማህበራዊ ጉዳይ ኤጀንሴ ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱረህማን ሙሳ ናቸው ፡፡
የችግሩን ስፋትና ውስብስብነት የሚመጥን ቅንጅታዊ አሰራር አስፈላጊ መሆኑን የገለጹጽ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ተሳፎ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድይፍራው ደጀኔ ፤ ዩኒቨርሲተው አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እንደሚሰራ በፓናል ውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ገልጸዋል፡፡
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን አስከፊ ችግር በማየት በኦስሪያ የዛሬ 75 ዓመት ህጻናቱን ሰብስበው ማሳደግ በጀመሩት ፕሮፌሰር ሔርማን ገማይነር የተመሰረተው ኤስ ኦ ኤስ በኢትዮጵያ ሃምሳ ዓመታትን አስቆጥሯል ፤ በ138 ሀገራት ውስጥም ህጻናት ላይ እየሰራ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡


