ሰኔ 25 ከጠዋቱ 1ሰዓት በድሬዳዋ አሸዋ የገበያ ስፍራ በደረሰው ድንገተኛ የእሳት አደጋ 1.7 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን የድሬዳዋ አስተዳደር መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ እና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በዛሬው እለት ለጋዜጠኞች በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
አደጋው በደረሰ ሰዓት የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር የአስተዳደሩ ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሀር ጨምሮ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ፣የጸጥታ መዋቅሩ፣ የሀረሪ ክልል እና መላ ህብረተሰቡ ያሳያው ርብርብ የሚደነቅ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አቶ ብሩክ ፈለቀ ተናግረዋል።
በተከሰተው የእሳት አደጋም በሰው ህይወት ላይ ጉዳት አለመድረሱን ገልጸዋል።
አደጋው ከተከሰተ በኃላም አስተዳደሩ የደረሰውን አደጋ በአግባቡ ለመምራት እንዲያስችል የተለያዩ ንዕሳን ኮሚቴ ተዋቅሮ የጉዳት ልየታ እና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የክቡር ከንቲባ ይፉዊ የድጋፍ ጥሪ ተከትሎ በርካታ ክልሎች ድርጅቶች እና ግለሰቦች የተሳተፉበት እና አጋርነታቸውን ያሳዩበት ገቢ የማሰባሰብ ስራ የተሰራበት መሆኑንም የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሙሺነር ጣሂር ሮብሌ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም አስተዳደሩ በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በጊዜያዊነት ተለዋጭ የቦታ ምችችት እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የንግዱ የማህበረሰብ ክፍሎች የምግብ ድጋፍ የማድረግ ስራ መሰራቱንም አብራርተዋል።
በደረሰው የእሳት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ በማድረግ ፤ ቦታው ድረስ በመገኝት ሀዘናቸውን በመግለጽ አብሮነታቸውን ላሳዩ ተቋማት፣ክልሎች ፣ድርጅቶች፣የሀይማኖት አባቶች፣ ግለሰቦች ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይም ተጎጂዎችን መልሶ ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።


