በድሬዳዋ አስተዳደር የምግብ ስርዓትና የኒውትሪሽን ካውንስል ተቋቋመ

በድሬዳዋ አስተዳደር የምግብ ስርአትና የኒውትሪሽን ረቂቅ ደንብን በዛሬው ዕለት ለካቢኔ ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን የድሬዳዋ አስተዳደር የስርአተ ምግብና የኒውትሪሽን ካውንስልም ተቋቁሟል፡፡

በመድረኩ የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በቀጣይ የካውንስሉን ስራ በተጠናከረ መልኩ መስራት እንደሚገባ የተናገሩ ሲሆን፤ ከምግብ ስርአት ጋር እንዲሁም ከኒውትሪሽን ጋር ተያይዞ በሁሉም ሴክተር ተቋማት ፎካል ፐርሰኖች / ባለሞያዎች/ ተመርጠው ስራዎችን እሰሩ መሆኑንና ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ዜጎች የምግብ ስርአት በኒውትሪሽን እንዳይጠቁ የሁሉንም ርብርብ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ከንቲባ ከድር በቀጣይ እንደ ሀገር አቀፍ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር የሚመራ ልዑካን ቡድን በድሬዳዋ እንደ አጠቃላይ በስርአተ ምግብና በሰቆጣ ዲክላሬሽን ላይ የተሰሩ ስራዎችን በተሞክሮነት ለመውሰድ በቢዮ አዋሌ ክላስተር ጉብኝት እንደሚያደርግ አመላክተው በዚህም ደግሞ ለእንግዶች ድሬዳዋን ሊመጥን የሚችልና ለሌሎች አካባቢዎች ተሞክሮ ሊሆን ሚችል ስራዎችን ማሳየት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው በስርአተ ምግብና በኒውትሪሽን እንዲሁም ከሰቆጣ ዲክላሬሽን ጋር ተያይዞ ግንዛቤ ፈጠራ ስራ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንደሚገባው አመላክተዋል፡፡ ጤናማነትና አምራችነት በቀጥታ የሚያያዘው ከአመጋገብ ጋር መሆኑንን የጠቆሙት ምክትል ከንቲባ ሀርቢ በቀጣይ ካውንስሉን የማጠናከር ስራዎች መሰራት እንደሚገባ ተናገረዋል፡፡

በተለይም የህፃናት መቀንጨርና መቀጨጭን ለመከላከል የአኗኗር ዘይቤን ቀይሮ ጤናማ ምግቦችን መመገብ ተገቢ መሆኑንና ለዚህ ደግሞ የኑሮ ውድነቱን ሊያቃልሉ የሚችሉ ስራዎች ማለትም ምርቶች በርካሽ ዋጋ እንዲሸጡ የማድረግ ስራዎች በአስተዳደሩ በኩል እየተሰሩ መሆንን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም አቶ ሀርቢ የከተማ ግብርናና የሌማት ቱሩፋት ስራዎች ላይ ተተኩሮ መሰራት እንደሚገባው እንዲሁም ከተረጅነት ወደ ምርታማነት መርሀ ግብርንም መጠቀም እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡

በሀገራችን በ2022 ከሁለት አመት በታች የሆኑ በምግብ እጥረት የተጎዱ ህፃናትን መጠን ዜሮ ለማድረግ መንግስት የሰቆጣ የቃል ኪዳን ስምምነት / ሰቆጣ ዲክላሬሽን/ ቃል የገባበት ሲሆን ይህንን ለመተግበር በሀገር አቀፍ ደረጃ በተመረጡ አካባቢዎች ላይ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡

እንደ ድሬደዋ አስተዳደር በሁለት ክላስተሮች በቢዮ አዋሌና በዋሂል ክላስተር በሰቆጣ ዲክላሬሽን የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ሲገኝ በ2017 ዓ.ም በአስተዳደሩ አንድ ተጨማሪ የጀልዴሳ ክላስተር ወደ ስራ እንደሚገባና በአጠቃላይም በ2017 ዓ.ም እንደ ድሬደዋ አስተዳደር ሶስት የሰቆጣ ክላስተሮች እንደሚኖሩ ከመድረኩ ተገልፆል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *