የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ከአሊ ቢራ ፋውንዴሽን እንዲሁም ከአሜሪካ ሚኒሶታ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር የስነ አእምሮ ጤና ላይ ያተኮረ ወርክ ሾፕ በዛሬው ዕለተ አካሄደ::
በመድረኩ የተገኙት የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ኃላፊ አቶ ሁሴን መሀመድ የዚህ ወርክ ሾፕ ዋንኛ አላማ ለማህበረሰቡ የስነ አእምሮ ጤና ላይ ግንዘቤ መፍጠር ነው ሲሉ አብራርተዋል:: በተለይም የበሽታውን የስርጭት መጠን ለመቀነስ ቅድመ ጥንቃቄ ላይ ተተኩሮ መሰራት እንደሚገባውም አቶ ሁሴን አመላክተዋል::
ከአሜሪካ ሚኒሶታ ዩኒቨርስቲ ተጋብዘው የመጡት ፕሮፌሰር ሙስጠፋ አል አብሲን በመድረኩ በጫት ዙሪያ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በአእምሮ ጤና አጠባበቅ ላይ በየጊዜው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን መፈጠር እንደሚገባ ተናግረዋል::
ፕሮፌሰሩ አያይዘውም በቀጣይ የአሜሪካ ሚኒሶታ ዩኒቨርስቲ ከድሬዳዋ ዩኒቨርስቲና ከአሊ ቢራ ፋውንዴሽን ጋር የሚሰራቸውን በጎ ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል::
በወርክ ሾፑ በአደንዛዥ እፅ ዙሪያ እንዲሁም የኢትዮጲያ የአእምሮ ጤናን በተመለከተና የህፃናትና የወጣቶች የአይምሮ ጤና ላይ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ከመድረኩ ሃሳብ አስተያየት ተሰቶበት ውይይት ተደርጓል::
በተያያዘ ዜናም በወርክ ሾፑ ማጠቃለያ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ መማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል የስነ አእምሮ ጤና ክፍል በድምቀት ተመርቋል::
ይህ የህክምና ማዕከልም ወደስራ መግባቱ በመስተዳደሩን የስነ አእምሮ ጤና ህክምና ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገው ተገልፇል::


