#ዜና የ5 ሚሊዮን የኮደርስ ስልጠና ለድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ልዩ በረከት ነው – ከንቲባ ከድር ጁሀር

#DGC መስከረም 18/2016

የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠና ኢንሸቲቭ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን የኦን ላይን ግብይት ለማቀላጠፍ መልካም እድል መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ”5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ” በ2026 አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ አንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስና በሰው ሰራሽ አስተውሎት መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት የማስጨበጥ አላማ ያለው ነው።

የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025ን እቅድ እውን በማድረግ የበለጸገች ሀገር ለመፍጠር የጎላ አበርክቶ እንደሚኖረውም ይታመናል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር፤ የ”5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ” ሰልጣኞችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል ጥሩ እድል መሆኑን ገልጸዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የተሰጠውን ኮታ በአግባቡ ለመጠቀም በመንግስትና በግል ተቋማት በቂ የቤተ ሙከራ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል።

የኮደርስ ስልጠናው በተለይም የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን የኦን ላይን ግብይት ለማቀላጠፍ መልካም እድል ይዞ የመጣ መሆኑንም ገልጸዋል።

የስልጠናው ተጠቃሚ መሆን የራስን የፈጠራ አቅም ከማሳደግ ባለፈ የቴክኖሎጂ አቅምን በማሳደግ ሀገራዊ ግቦችን ማሳካት የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በተለይም ወጣቶች የቴክኖሎጂ አቅማቸውን በማሳደግ በኦን ላይን ኮሙኒኬሽን ተጨማሪ ገቢ ማመንጨት የሚችሉበትን እድል የሚፈጥር መሆኑንም አስረድተዋል።

በመሆኑም ወጣቶች የቴክኖሎጂና የፈጠራ ክህሎታቸውን በማዳበር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን እድል በአግባቡ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 አካል የሆነው የ”5 ሚሊዬን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ” የዲጅታል ክህሎትን ለማሳደግ በኢትዮዽያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግሥታት የተጀመረ የትብብር ፕሮጀክት መሆኑ ይታወቃል።

ምንጨ፦ኢዜአ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *