ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት እንደ መሆኑ የሰላም አደረጃጀቶችን ይበልጥ እያጠናከሩ መሄድ እንደሚገባ ተገለፀ::

በድሬዳዋ አስተዳደር የሰላም ምክር ቤት ለማቋቋም የሚያስችል የባለድርሻ አካላት የቅደመ ዉይይት የጋራ መድረክ ተካሂዷል።

እንደ ሀገር በሰላም ሚንስትር ተዘጋጅቶ በሁሉም ክልልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ሁሉንም ባለ ድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ እየተቋቋመ ያለዉ የሰላም ም/ቤት በድሬዳዋ በይፋ ለማቋቋም ቅደመ ዝግጅቶች ሲደረጉ የቆዩ ሲሆን ከእዚህም ዉስጥ የጋራ የቅደመ ዉይይት መድረክ ዋንኛዉ ነዉ።

ይህንንም ተከትሎ በሰላም ም/ቤት ማቋቋሚያ ደንብ ዙሪያ ሁሉንም የህ/ብ ክፍልና ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ሁለተኛ ዙር የዉይይት መድረክ የተካሄደ ሲሆን በመድረኩ የተገኙት የድ/ዳ ፍትህ ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ አብዱሰላም አህመድ የሁሉም ነገር መሠረት ሰላም እንደመሆኑ የአስተዳደሩንም ሆነ የሀገር ሰላም ይበልጥ ጠብቆ ለማስቀጠል የሰላም አደረጃጀቶች ማቋቋምና እያጠናከሩ መሄድ ወሳኝ መሆኑን ነዉ የገለፁት።

ለእዚህም ሁሉም የህ/ብ ክፍልና ባለ ድርሻ በባለቤትነት ያሳተፈ የሰላም ም/ቤት በአስተዳደርና በታችኛዉ የወረዳና የቀበሌ መዋቅር በይፋ እንደ ሚቋቋም ተናግረዉ መላዉ የአስተዳደሩ ነዋሪ ሁልግዜም ለሰላሙ ቅድሚያ በመስጠት ለድሬዳዋ ሰላም መረጋገጥ እያደረገ ላለዉ አስተዋፆና ተኪ የለሽ ሚና ምስጋናቸዉን አያይዘዉ አቅርበዋል።

በዉይይት መድረኩ ቀደም ብሎ በነበሩ የዉይይት መድረኮች የተሰጡ ግብአቶችን ባካተተ መልክ የሰላም ም/ቤት ማቋቋሚያ ደንብ በተቋሙ ከፍተኛ የህግ ባለሞያ የቀረበ ሲሆን የመድረኩ ተሳታፊዎችም ሰፊ ዉይይት በማድረግ የሰላም ም/ቤቱ መቋቋም ለዘላቂ ሁለተናዊ ሰላም መረጋገጥ ወሳኝ ነዉ ያሉ ሲሆን ለእዚህም የድርሻቸዉን እንደሚወጡ ነዉ የገለፁት።

በእዚሁ ለሁለተኛ ግዜ የሰላም ም/ቤት ለማቋቋም በተካሄደዉ የባለድርሻ አካላት የቅድመ ዉይይት መድረክ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሸማግሌዎች፣ የማ/አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ም/ቤት፣ የወጣትና የሴት አደረጃጀት አመራርና ተወካዮች የወረዳ የፀጥታ ሀላፊዎች እንዲሁም የሰላም ክበባትና የተለያዩ የህ/ብ ክፍል ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

ምንጭ፦የፍትህ ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *