በትግራይ ክልል ተዘግተው የነበሩ 227 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ገብተዋል፦ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

በኢንዱስትሪ ዘርፍ በበጀት አመቱ 9.2 በመቶ እድገት የተመዘገበ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከፍተኛ እና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ንዑስ ዘርፍ 10.2 በመቶ ማደጉን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ገለፁ።

እየተካሄደ በሚገኘው በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ በአብላጫ ድምጽ አዲስ የተሾሙት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ለምክር ቤቶቹ የመንግስትን የ2016 ዓ.ም አፈፃፀም እና የ2017 ዓ.ም የመንግስት አቅጣጫ በማቅረብ ላይ ናቸው።

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት እና የዘርፉን ልማት በዘላቂነት ለማረጋገጥ “ኢትዮጵያ ታምርት” የተሰኘው እንቅስቃሴ ተቋሟዊ በሆነ አግባብ ተግባራዊ በመሆን ላይ ይገኛል።

በዚህ እንቅስቃሴ መሰረት በተወሰኑ ተጨባጭ ርምጃዎች የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የማምረት አቅም 59 በመቶ ደርሷል። የአገር ውስጥ ገበያ ድርሻው 40 በመቶ ሲደርስ 2.8 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የማኑፋክቸሪንግ ገቢ ምርትን ለመተካት ተችሏል።

በተጨማሪም አምራችነትን በያካባቢው ለማስፋፋት በተደረገው ጥረት በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ ከማምረት ውጭ ከነበሩት 446 አምራች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ 395 ኢንዱስትሪዎች ማለትም 126 አነስተኛ፣ 193 መካከለኛ እና 74 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደስራ እንዲመለሱ ተደርገዋል።

በትግራይ ክልል በተደረገው ክትትል እና ድጋፍ ተዘግተው ከነበሩት አምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል 227 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ገብተዋል።

ባጠቃላይ እነዚህ እርምጃዎች በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት ዘርፉን ለማሳግ የመንግስትን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ናቸው።

#etv#EBC

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *