በድሬዳዋ የትምህርት ጥራትና ፍትሃዊ ተደራሽነትን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች የተገኙ ውጤቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል – የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሃር

በድሬዳዋ የትምህርት ጥራትና ፍትሃዊ ተደራሽነትን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች የተገኙ ውጤቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የአስተዳደሩ ከንቲባ የተከበሩ ከድር ጁሃር ተናገሩ።

33ኛው የድሬዳዋ አስተዳደር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ ተካሂዷል።

“የላቀ ትጋት፤ ለትምህርት ጥራት” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በተካሄደው የትምህርት ጉባኤ ላይ በትምህርት ዘርፍ ለተገኙ ለውጦችና ውጤቶች አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት፣ የትምህርት አጋሮች፣ መምህራን፣ ትምህርት ቤቶች እና ወላጆች ዕውቅናና ሽልማት ተበርክቷል።

በተጨማሪም በአስተዳደር አቀፍ የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ፈተናዎች እንዲሁም በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የላቀ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቷል።

በሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሃር

ሀገር አቀፉን ለውጥ ተከትሎ በአስተዳደሩ ገጠርና ከተማ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እና ፍትሃዊ ተደራሽነትን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በተለይ በማህበረሰብ ንቅናቄ፣ በባለድርሻዎችና በባለሃብቶች ድጋፍ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል እና ትምህርት ቤቶችን ማራኪ ሥፍራ በማድረግ የተገኙ ለውጦች ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ መሠረታዊ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል።

እነዚህ ሥራዎች አዲሱን የትምህርት ስርአት በተቀናጀ መንገድ በመተግበር፣ ዲጂታል የመማር ማስተማሩን ስራ በማስፋት፣ በትምህርት ቤቶች የምገባ መርሃ-ግብር በስፋት በማካሄድ ተጨባጭ ለውጦቹ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማስቻላቸውንም ተናግረዋል።

በዘንድሮ ዓመትም የመምህራንን አቅም በማጎልበትና የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እና በገጠርና ከተማ ፍትሃዊ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት ርብርቡ ተጠናክሮ ይቀጥለል ብለዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጠን አልይ በበኩላቸው በተጠናቀቀው ዓመት የዲጂታል ቴክኖሎጂን በሥራ ላይ በስፋት በመጠቀም፣ የቤተ ሙከራ እና የቤተ መጻህፍት ተደራሽነትን በማስፋት ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት የተከናወኑ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ለውጦች እንዲመዘገቡ አግዘዋል ነው ያሉት።

ትውልዱ ለፈጠራና ለምርምር የሚያነሳሱ ዕውቀትና ክህሎት እንዲጨብጥ የተቀናጁ እና የተናበቡ ስራዎች መጀመራቸው በሳይንስና በሒሳብ ትምህርቶች እንዲሁም በቴክኖሎጂ ዘርፍ ብቁ ዜጎችን ለማፍራት እያስቻለ መሆኑንም አስረድተዋል።

ዘንድሮም ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር በትምህርት ጥራት ላይ የተሻለ ለውጥ ለማስመዝገብ በትጋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ የተሰጠው የዕውቅናና የሽልማት የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን ወደ ላቀ ከፍታ ለማሳደግ እንደሚያስችልም አመልክተዋል።

በስነስርዓቱ ላይ ዕውቅናና ሽልማት የተሰጣቸው ተቋማት፣ መምህራን እና ወላጆች በቀጣይ በቅንጅት የጀመሯቸውን ሥራዎች አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ዛሬ በተካሄደው 33ኛው የትምህርት ጉባኤ ላይ የአስተዳደሩ የካቢኔ አባላት፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና በትምህርት ዘርፍ የሚሰሩ የልማት አጋሮች ተሳትፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *