የህዳሴው ግድብ “የዘመናት ህልም ተምኔት ወደ የሚጨበጥ ስኬት የተቀየረበት እና የራሳችንን የእድገት ህልም በራሳችን አቅም ልንፈታ እንደምንችል ለዓለም ያሳየንበት” ነው- ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ንግግራቸው የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን ከሚያመላክቱ ክዋኔዎች አንዱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ለግድቡ እዚህ መድረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የነበረው ሚና እጅግ የላቀ እና በክብር መዝገብ ውስጥ በወርቅ ቀለም ተፅፎ በታሪክ የሚቀመጥ እና የሚወደስ ይሆናል ብለዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ከፍፃሜው እንደሚደርስ በልባቸው ተማምነው መቀነት ከመፍታት እስከ ውጭ ምንዛሬ ማበርከት አስተዋፆ ላደረጉ ዜጎች ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የህዳሴው ግድብ ለኢትዮያውያን የኤሌክትሪክ ማመንጫ ኃይል ብቻ ተብሎ የሚቀመጥ ሳይሆን “የዘመናት ህልም ተምኔት ወደ የሚጨበጥ ስኬት የተቀየረበት እና የራሳችንን የእድገት ህልም በራሳችን አቅም ልንፈታ እንደምንችል ለዓለም ያሳየንበት” ነውም ብለዋል፡፡

ግድቡ ቱሪዝምን፣የውሃ ውስጥ ሀብትን፣የአካባቢ ሚዛን መጠበቅን ፣የሞራል ልዕልና እና የህብረ ብሔራዊ አንድነትን ሁሉ ያቀፈ ነው ሲሉም ፕሬዚደንት ታዬ አጽቀሥላሴ በንግግራቸው አንስተዋል፡፡

ታላቁ ህዳሴ ግድብ የጎረቤት ሀገራትን የመልማት ፍላጎት የሚደግፍ እና የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን ስጋት የሚቀርፍም ጭምር ነውም ብለዋል፡፡

EBC

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *