ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እውን፣ ገቢር እና ገበያ መር እየሆነ በዓለም ተወዳዳሪ እንዲሆን መሰረቱን ከነጠላ ዘርፍ ተኮርነት ወደ ብዙሃን ዘርፍ ኢኮኖሚ እያሸጋገረ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የህዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መሰረት እየጣለ እንደሚገኝ ጠቅሰው በ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ውስጥ ለማከናወን የተያዙ ዕቅዶችን ለማሳካት አወንታዊ አቅጣጫ እንደያዘ አመላካች ነው ብለዋል።
በ2016 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 1 በመቶ ጥቅል ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ መቻሉን ፕሬዚደንቱ ጠቅሰዋል።
የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ስጋቶችን እና ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ተጨባጭ ውጤቶችን እያመጣ ስለመሆኑ አመላካች ነው ብለዋል።
የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 13.8 በመቶ እድገት ያሳየ መሆኑን በመግለጽ፤ በዚህም 3.9 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ፍሰት መመዝገቡን ጠቅሰዋል።
በበጀት ዓመቱ ለ4 ሚሊዮን 250 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል ያሉት ፕሬዚደንቱ ከዚህ ውስጥ የውጭ ሀገር የስራ ዕድል ስምሪት እና ሕጋዊ ማዕቀፍ በማስያዝ 379 ሺህ ዜጎች የውጭ ሀገር የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በሸቀጦች ወጪ ንግድ እና በአገልግሎት የውጭ ንግድ የታየው እድገትም ሀገሪቱን የኢኮኖሚ ስብራቶችን ለመጠገን የምታደርገው ጥረት በመልካም ጎዳና ላይ እንደሚገኝ አመላካች ነው ብለዋል።
የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር መንግስት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ከአቅርቦት አንጻር በምርት እና ምርታማነት ላይ ያተኮሩ ስራዎች ተጀምረው የዋጋ ግሽበትን ትርጉም ባለው መልኩ መቆጣጠር እንዳስቻሉ ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የነሐሴ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 17.2 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን ጠቅሰው ይህም በ2015 ነሐሴ ወር ከተመዘገበው 28.8 በመቶ አጠቃላይ ዋጋ ግሽበት አንጻር ሲታይ ዝቅ ያለ ስለመሆኑ ነው ያነሱት።
EBC


