በድሬዳዋ አስተዳደር የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የድህረ ተከላ እና የደን እንክብካቤ ስራ ተካሄደ።

#DGC ህዳር 22/2017

በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የጂኦግራፊ እና አካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ከአስተዳደሩ አካባቢ ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ጋር በመተባበር በዋሂል ክላስተር ሃርላ ገጠር ቀበሌ ቀደም ብለው የተተከሉ ችግኞችን በድህረ ተከላ የእንክብካቤ ስራዎችን አከናወኑ።

በአስተዳደሩ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃግብር እስካሁን ከ2.4 ሚሊየን በላይ የደን ፣ የውበት እና የጥምር ደን ችግኞችን በሁሉም የከተማ እና ገጠር ክፍሎች መተከላቸውን የተገፀ ሲሆን በዛሬው መርሃግብርም የእንክብካቤ ስራዎች ተከናውነዋል።

ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ የሚሰለጥኑ ተማሪዎችን ከቃል ትምህርት በዘለለ በተግባር የተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና እንክብካቤ ተግባራቶች ላይ ወርደው እንዲሳተፉ በማድረግ የበኩላቸውን አበርክቶ እንዲያኖሩ መሰራቱን በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የጂኦግራፊ እና አካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር እና የትምህርት ክፍል ሃላፊ አቶ ከፈለኝ ቸርነት በመርሃግብሩ ወቅት አስረድተዋል።

አክለውም በረሃማነትን ለመታደግ እና መሬትን ለማከም ችግኞችን ከመትከል ባሻገር ተደጋጋሚነት ያለው እንክብካቤ በማከናወን የደን ሽፋንን ማሳደግ እንደሚቻል ገልፀዋል።

በድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የደን ልማት ቡድን መሪ አቶ ማሙሽ ዘውዱ እንዳስረዱት የአየር ንብረት ለውጥን ለመታደግ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን መንከባከብና ወደ ደንነት መቀየር ትልቁ ግብ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አያይዘውም ህብረተሰባችን ዝናብ በማይኖርባቸው ደረቅ ወቅቶች ቀድም ብለው የተተከሉ ችግኞችን እንዲንከባከብ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ነሐሴ 17 2016 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል አሻራችንን እናኑር በሚል መሪ ሃሳብ በመላ ሀገሪቱ በተካሄደው ህዝባዊ ተሳትፎ ወቅት በአስተዳደሩም የሃርላ ገጠር ቀበሌ ላይ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር መከናወኑ ይታወሳል።

በመርሃግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው የጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ፣ መምህራን ተሳትፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *