የድሬዳዋ አስተዳደር የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የረመዳን እና የአብይ ፆምን ምክንያት በማድረግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ 550 የማህበረሰብ ክፍሎች በ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጪ የምግብ ፍጆታዎችን በዛሬው እለት ድጋፍ አድርጓል ።
ድጋፍንም የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሀርን ጨምሮ በብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ እና ከፍተኛ የአስተዳደሩ አመራሮች በተገኙበትም ነው ድጋፍ የተደረገው።
ሰው ተኮር የሆነው ብልፅግና ፓርቲ ለዝቅተኛ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚደረጉ ድጋፎች የአብሮነትንና የመደጋገፍ ባህልን ከማሳደግ አንጻር ትልቅ ሚና እንዳላቸው የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ገልፀው በቀጣይም መሰል ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ነው ያስታወቁት ።
የድሬደዋ አስተዳደር አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሱሌማን አሊ በበኩላቸው በ 3 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ወጪ 550 ለሚጠጉ የማህበረሰብ ክፍሎች የምግብ ድጋፉን ኮሚሽኑ ማድረጉን ገልጸው በቀጣይም 600 ለሚሆኑ ገጠር ነዋሪዎች መሰል ድጋፍ እንደሚቀጥልም ነው ያስታወቁት።
በአለማየሁ አበበ
ፎቶ :- አገኘው ሸዋረጋ


