የ1446ኛው ዓመተ ሂጅራ የረመዳን ወር ጾምን በማስመልከት የክርስትና እምነት ተከታዮች ለእስልምና እምነት ተከታዮች በለገሀሬ ጎዳና ላይ ደማቅ የኢፍጣር መርሀግብር አካሂደዋል።
ሙስሊም ክርስቲያኑ ለዘመናት ያቆዩት የአብሮነት፣የፍቅር፣ የአንድነት እና የስምምነት ምልክት ሆና የምትጠቀሰው ድሬዳዋ ዛሬም ወንድማማች እና እህትማማችነትን በማጠናከር ደማቅ ታሪክ በመስራት ላይ ትገኛለች።
በመርሀ ግብሩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ክቡር አቶ ሀርቢ ቡህ በዚህ የአንድነት የአብሮነትና የወንድማማችነት ምስክር በሆነበት ቀን ተገኝተው ንግግር በማድረጋቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
አስተዳደሩ ከመቼው ጊዜ በላይ ሰላም እና ጸጥታዋ የተረጋገጠ ለነዋሪዎቿ ምቹ በመሆን በተለይም ማህበራዊ ትስስሩን በማጎልበት በኩል ዘርፈ ብዙ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ይህንንም ማህበራዊ መስተጋብሮች ባህል አድርጎ ማስቀጠል ይገባልም ሲሉ ነዉ ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ አጽኖት የሰጡት።
በብልጽግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅ/ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት አቶ ደረጄ ጸጋዬም በበኩላቸው በህዝበ ክርስቲያኑ የዓብይ ጾም በሙስሊሙ ታላቁ የረመዳን ወር ጾም መግባቱን ተከትሎ የእርስ በእርስ አብሮነቱ አንድነቱ መተሳሰቡ ይበልጥ የሚጠነክርበት ወቅት መሆኑን ጠቅሰው ይህንንም በሌሎች የልማት ስራዎች መድገም ይገባል ብለዋል።
በመርሀግብሩም የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ኡጋዞች፣ አባገዳዎች፣ኡስታዞች ፣የወረዳ አመራሮች እንዲሁም በርካታ ነዋሪዎች ተገኝተዋል ።
ሰላም ለማ
ምስል ፦ አገኘው ሸዋረጋ


