በዛሬው ዕለት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት የካሳ ክፍያ መልሶ ማቋቋም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መሀመድ ጃማ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በወረዳ 01 መልካ ጀብዱ በመንገድ መሰረተ ልማት እንዲሁም በኮሪደር ልማት ምክንያት ከይዞታቸው ለተነሱ 261 የልማት ተነሺዎች በአስተዳደሩ በተወሰነው ልዩ ውሳኔ መሰረት የካሳ ክፍያቸው ከዛሬ መጋቢት 12/2017 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚከፈል ገልፀዋል፡፡
አቶ መሀመድ አያይዘውም ማህበረሰቡም ከንቲባ ፅ/ቤት ካሳ ክፍያ መልሶ መቋቋም ዳይሬክቶሬት ክፍል ከወረዳ 01 የይዞታ ማረጋገጫን፣ የነዋሪነት መታወቂያን እንዲሁም የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ የሂሳብ ደብተር ኮፒ አድርገው በማምጣት አሸራ ሰተው ክፍያቸውን መውሰድ እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡
የካሳ ክፍያውም ከዚህ ቀደም በነበረው ግምት ሳይሆን ማሻሻያ መደረጉን የገለፁት ዳይሬክቶሬቱ በዚህም ማህበረሰቡ የተገመተለትን የካሳ ክፍያ ግልፅ በሆነ መልኩ እንዲያቅ የተደረገ መሆኑን ገልፀው፤ ምትክ መሬት ማግኘት ያለባቸውም በድሬዳዋ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በኩል እዛው አካባቢ 31 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ የሽንሸና ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የመልካ የልማት ተነሺዎች ልማት ወዳዶች እንዲሁም ለድሬዳዋ እድገት ቅድሚያ በመስጠት ከልማቱ ጎን በመቆም የበኩላቸውን መወጣታቸውን ዳይሬክቶሬቱ ተናግረው፤ እስከ ዛሬ ካሳ ሳይከፈላቸው በልማት ወዳድነትና በትግስት ስለጠበቁም አመስግነዋል፡፡
በመጨረሻም አቶ መሀመድ ድሬዳዋ በአገር አቀፈ ደረጃ የኢንዱስትሪ እና የአገልግሎት ዘርፍ መናሃሪያ ለማድረግ በሚደረገው ጥርት የካሳ ተነሺዎች እያደረጉት ያለው ድግፍ መቀጠል ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በኤደን ሳሙኤል
ፎቶ፤-ሰላም አበበ


