በኢትዮጵያ የብስክሌት ስፖርት ውድድር ታሪክ ውስጥ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የጥሎ ማለፍ የታዳጊዎች ውድድር በድሬዳዋ ተከናወነ

የፈናን ፔይ የብስክሌት ሻምፒዮና የጥሎ ማለፍ ጫወታ አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ባጠናቀቁት በአቤኔዘር አለሙና እና ኢሳኮር ፍሬው መካከል የታየው ፉክክር በስፍራው ከታደመው የስፖርት አፍቃሪ እና ተመልካች ከፍተኛ አድናቆት ተችሮታል።

አርባ ሁለት ዙሮችን በሚሸፍነውና በያንዳንዱ ዙር መጨረሻ የሆነ ተወዳዳሪ ከጫወታ ውጪ እየሆነ የመጨረሻዎቹ ሁለት ተወዳዳሪዎች እስኪቀሩ ድረስ ጠንካራ ፣ አጓጊና ብርቱ ፉክክር በታየበት በዚህ በአራተኛው ቀን የፈናን ፔይ የታዳጊዎች ብስክሌት ሻምፒዮና ፣በአለማቀፍ ደረጃ እና በኦሎምፒክ ተወዳጅ የሆነ የብስክሌት ስፖርት ውድድር ዓይነት ሲሆን በኢትዮጵያና በድሬዳዋ ደረጃ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ መሆኑን የዝግጅቱ አዘጋጅ አቶ ቢኒያም ነገሱ ገልጸዋል።

በድሬዳዋ ምድር ባቡር ፊትለፊት በተካሔደው በዚህ የታዳጊዎች የጥሎ ማለፍ የብስክሌት ውድድር በስፍራው ተገኝተው የተከታተሉ የብስክሌት ስፖርት አፍቃሪያን ፣ የብስክሌት ስፖርት ባለሞያዎችና ዳኞች እንዲህ ዓይነቱ የጥሎ ማለፍ ውድድር የመጨረሻ መስመር ፈጣን ተስፈንጣሪ አቅምና ብቃት ያላቸውን ተወዳዳሪዎች ብቃትና አቅም ከመገንባት ባሻገር በተወዳዳሪዎች መካከል የሚደረገው ጠንካራ ፉክክር የሚታይበት እንደመሆኑ የተመልካችን ቀልብ የሚስብና የሚማርክ የውድድር ዓይነት ነው ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል ።

ውድድሩን ሲከታተሉ የነበሩ የስፖርቱ አፍቃሪያን በአስተያየታቸው፣ የድሬ ቱዩብ እና ሐሪፍ ስፖርት ባለቤት የሆኑት ወጣት ቢኒያም ነገሱ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ በማፍሰስ የቶቶ ብስክሌት ክለብን በማቋቋም ፣ የብስክሌት ስፖርት አካዳሚ በመክፈትና ታዳጊዎችን በማሰልጠን ፣ በትጥቅና ሎጀስቲክስ በመደገፍ ፣ ሀገር አቀፍ ውድድሮችን ድሬዳዋን ጨምሮ በሌሎች የክልል ከተሞች በማዘጋጀት ፣ እንደዚሁም ድሬዳዋንና ሀገራቸውን በመወከል በአለማቀፍ የብስክሌት ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ወጣቶችን በመደገፍ ለስፖርቱ እድገት እያደረጉት ያለው አስተዋጾ ሊያስመሰግናቸው እንደሚገባ ገልጸው ፣ ሌሎች በርካታ ድሬዳዋ ያፈራቻቸው ባለሀብቶች ትውልድን በማነጽ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ባሉት እና የድሬዳዋ የደመቀ የስፖርት ታሪክ በሆነው የብስክሌት ስፖርት ላይ የራሳቸውን ድርሻና አሻራ ሊያሳርፉ የሚችሉበትን ይህን ወርቃማ እድልና አጋጣሚ ቢጠቀሙት መልካም ነው ብለዋል።

ይህ በቶቶ ብስክሌት አካዳሚ ውስጥ ታቅፈው ስልጠና እየወሰዱ በሚገኙ ታዳጊዎች መካካል እየተደረገ ያለው የፈናን ፔይ የብስክሌት ሻምፒዮና የጥሎ ማለፍ ጫወታ አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ባጠናቀቁት በአቤኔዘር እና ኢሳኮር መካከል የታየው ፉክክር በስፍራው ከታደመው የስፖርት አፍቃሪ እና ተመልካች ከፍተኛ አድናቆት ተችሮታል።

ይህ ከነሐሴ 6 ቀን ጀምሮ እየተካሔደ የሚገኘው የፈናን ፔይ ሻምፒዮን የታዳጊዎች የብስክሌት ውድድር በነገው እለት እሁድ ነሐሴ 11 ቀን በከዚራ ምድር ባቡር ፍጻሜውን ያገኛል ።

የዚህ ሻምፒየን አሸናፊዎች ወደ መደበኛ የሳይክልስ ኮርስ ቡድኖች የሚሸጋገሩበት ከመሆኑም በላይ ሌሎች ተተኪዎችን ወደ ስፖርቱ እንዲሳቡ የሚያነሳሳ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የማበረታቻ ሽልማት መዘጋጀቱንም የፈናን ፔይ ሻምፒዮና አዘጋጆች ገልጸዋል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *