የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተገለፀ

የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የ2017 በጀት አመት እቅድ ክንውንና የ2018 እቅድ የባለድርሻ አካላት ምክክር እንዲሁም ”ፅዱ ኢትዮጵያን እስከ ባህል” የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።

የባለስልጣኑ ኃላፊ ተወካይ አቶ ማስረሻ ይመር የአየር ንብረት ለውጥ በአለም አቀፍ ደረጃ የሰው ልጆችን እየፈተኑ ከሚገኙ ቀውሶች አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።

እንደሀገር የአካባቢ ብክለት ችግር የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በዘላቂነት በፖሊሲና ስትራቴጂ የተደገፉ ስራዎች ህብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን ባማከለ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን አውስተዋል።

በተለይም ”ፅዱ ኢትዮጵያን እስከ ባህል” በሚል መሪ ቃል ለስድስት ወራት የሚቆይ የአካባቢ ብክለት መከላከል ንቅናቄ እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን ዘንድሮም ለሁለተኛ ጊዜ ንቅናቄው ከሰኔ ወር በመጀመር የፕላስቲክ ቆሻሻ ብክለት መከላከል፣በሐምሌ ወር የአፈርና ውሃ ብክለት መከላከል ጉዳዮች እተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

በነሐሴ ወር የአየር ብክለትን በተመለከተ በባለስልጣን መ/ቤቱ የአካባቢ ህግ ተከባሪነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዮናስ በፍቃዱ በአየር ብክለት ምንነት፣ምንጮች፣ የሚያስከትለው ጉዳትና መከላከያ ዘዴዎች ላይ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበው ተሳታፊዎች እንዲወያዩበት እና ባለስልጣን መ/ቤቱና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ሊያከናውኗቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች በስፋት ተነስተዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የአካባቢ ህግ ተከባሪነትና የአካባቢና ማህበራዊ ተፅእኖ ግምገማ ቡድን መሪ አቶ ደረጀ አቢቲ የአየር ብክለትን በመከላከል ሂደት በአንድ አካል ብቻ የሚከናወን ባለመሆኑ ህብረተሰቡ ብሎም ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

‘ፅዱ ኢትዮጵያን እስከ ባህል” በሚል መሪ ቃል እየተከናወነ በሚገኝው ንቅናቄ በአየር ብክለት ዙሪያ ግንዛቤ የመፍጠር ተግባር ትኩረት ተሰቶት እየተከናወነ እንደሚገኝ ይህም ሁሉም አካል ስለጉዳዩ በቂ ግንዛቤ ኖሮት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት እንደሚያግዝ ገልፀዋል።

በንቅናቄው በነሐሴ ወር የአየር ብክለት ጉዳይ ዋና አጀንዳ ተደርጎ የምክክር መድረክ እንዲሁም ህግ የማስከበር እርምጃዎች እየተሰራ እንደሚገኝ ጉዳዩን በተመለከተ በተለያዩ መንገዶች የሚከናወኑ ስራዎች ችግሩን በጋራ ለመከላከል አቅም እንደሚፈጥር አቶ ደረጀ አክለው ገልጸዋል ።

በመድረኩ የባለስልጣኑ የ2017 ዓ .ም እቅድ ክንውን እንዲሁም የ2018 ዓ .ም እቅድ ለባለድርሻ አካላት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበት የጋራ መግባባት ተደርሶበታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *