በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) በተፃፈው በመደመር ትውልድ መፅሀፍ ሽያጭ እንዲሁም በአስተዳደሩ ድጋፍ ዘመናዊና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለተገነባው እመርታ ቤተ-መፅሀፍ ግብአት ማሰባሰቢያ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ተካሄደ።
በዚህም በመርሃ-ግብሩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ተወካይ እና የከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁን ሁሉም ተቋማት እንዲሁም በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የሚገኙ የድሬዳዋ ወዳጆችና ደጋፊዎች ለቤተ-መፅሀፉ የመፅሀፍት እና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍት እና ቤተ-መዛግብት ተወካይ አቶ እስራኤል በዙ በበኩላቸው ተቋማቸው ቤተጻህፍቱን ይበልጥ ለማደራጀት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
የአብርሆት ቤተ-መፅሃፍት ተወካይ አቶ እንዳልካቸው መኮንን በበኩላቸው የእምርታ ቤተ መጻሕፍት የአብርሆት ቤተ-መፅሃፍትን ፈለግ በመከተል በክልሎች ደረጃ ከኢትዮጵያ ግንባር ቀደም መሆኑን ተናግረው በቀጣይም ተቋማቸው በመፅሀፍት ብቻ ሳይሆን በስልጠና እና በማደራጀት ከቤተ-መፅሃፍቱ ጎን እንደሆነ ተናግረዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ባህል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ወንደሰን አባይ በበኩላቸው የእምርታ ቤተ-መፅሀፍ በ475 ሚሊዮን ብር የተገነባ መሆኑን ገልፀው፤ ፕሮጀክቱ ከተያዘለት 18 ወራት ቀደም ብሎ በ5 ወራት ለማጠናቀቅ መቻሉን ገልፀዋል።


