የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት
ሀገር አቀፍ የህግ ተርጎሚዎች መድረክ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረትን ጨምሮ ሁሉም የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች በተገኙበት በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በዚህም በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ተወካይ እና የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሙሉካ መሀመድ በድሬዳዋ አስተዳደር በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ የዳኝነት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀው፤በአስተዳደሩ ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን በአዋጅ በማደራጀት ወደ ስራ እየተገባ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
በመድረኩ በፌዴራል እና በክልል ፍርድ ቤቶች የለዉጥ ፍኖተ ካርታ አፈጻጸም ወቅት የታዩ መልካም ተሞክሮዎች እና ተግዳሮቶች፣ የዳኝነት አገልግሎትን ዲጂታላይዝ ለማድረግ በፌዴራልም ሆነ በክልል ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ የተደረጉ ቴክኖሎጂዎች አይነት እና መጠን እንዲሁም በሁሉም ክልሎች ሊስፋፋ የሚቻልበት አግባብ ላይ ውይይት እንደሚደረግ የገለፁት ደግሞ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ናቸው።
ከዚህ ቀደም በነበረው የግንኙነት መድረክ ውይይት ተደርጎባቸው ተከናውነው እንዲቀርቡ አቅጣጫ የተሰጠባቸው ጉዳዮችን የተመለከተ የአፈጻጸም ሪፖርት እንደሚቀርብም ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ጠቁመዋል።
በመጨረሻም የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታላይዝ በማድረጉ ረገድ እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት አመላክተዋል።


