የብልፅግና ፓርቲ የ2018 ዓ.ም ዓመታዊ የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና የአመራር አባላቱን አቅም የሚገነቡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑ ይታወቃል።
“በመደመር መንግሥት ዕይታ፤ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሐሳብ በተሰጠው ስልጠና ላይ ከ2ሺህ በላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ከስልጠናው በተጓዳኝ በመዲናዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
የወንዝ ዳርቻ ልማትን ጨምሮ በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች የእይታ ለውጥ እና የአመራር ቁርጠኝነት የታየባቸው መሆኑ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ የከፍታ ጉዞ የኢትዮጵያን ገፅታ እየቀየረ እንደሚገኝም ተመላክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በመዲናዋ ህዝብን በማሳተፍ የተከናወኑ የልማት ተግባራት ውጤት አምጥተዋል፡፡
በዚህም አዲስ አበባን በአፍሪካ ተጠቃሽ ያደረገ ውጤቶች የተገኘበት ነው ብለዋል።
በቤት ልማትና አቅርቦት ላይ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ የተከናወኑ ስራዎች አቅርቦቱን ለማሳደግ ማስቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
በተሰሩ ስራዎች በርካታ አቅመ ደካሞች ቤት ማግኘታቸውን የገለጹት ከንቲባዋ፤ በትምህርት ቤት ምገባ መርኃ ግብር ውጤት መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡
በመዲናዋ ህጻናትንና ወጣቶችን ታሳቢ ያደረጉ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ መፍጠርና መፍጠን መርህን በመከተል ርብርብ እየተደረገ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡


