በዚህም በስልጠና መድረኩ የተገኙት የስዊፍት ትራንስፖርት ስራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ አሸብር ስዊፍት ትራንስፖርት የትራንስፖርት ችግርን ለመቅረፍ በርካታ የኤሌትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማቅረብ ለተጠቃሚዎች እያከፋፈለ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ስዊፍት ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎችን ከማቅረብ በተጨማሪ ተሽከርካሪዎቹ አዲስ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ስለመኪኖቹ አጠቃቀም፣ ስለ መሰረታዊ የጥገናና የአነዳድ ሁኔታ እንዲሁም ስለ ደህንነት አጠባበቅ ላይ በዛሬው ዕለት ለአሽከርካሪዎች፣ ለመንገድ ትራንስፖርት ተወካዮች እንዲሁም በአጠቃላይ ለባለድርሻ አካላት ስልጠና መሰጠቱን አቶ ብሩክ ተናግረዋል።
ተሽከርካሪዎቹ አዲስ እንደመሆናቸው የጥገና ማዕከላት (ጋራዥ) አለመኖሩን ስራ አስኪያጁ አንስተው ተቋሙም ይህንን ታሳቢ በማድረግ ሶስት ሰራተኞችን ወደ ቻይና በመላክ ያሰለጠነ መሆኑን ያብራሩ ሲሆን አሁን ላይ ባለሞያዎቹ በወሰዱት ስልጠና መሰረት በመኪኖቹ ዙሪያ ለሚፈጠሩ የቴክኒክ ችግሮች አስፈላጊውን መረጃ በመስጠት እገዛ ለማረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በመጨረሻም አቶ ብሩክ በቅርቡ ሰፊ የጥገና ማዕከል ተቋቁሞ አስፈላጊውን የጥገና እና ተያያዥ ስራዎችን መሰራት እንዲጀምር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ያመላከቱ ሲሆን፤ ለአሽከርካሪዎች እና ለባለድርሻ አካላትም ስልጠና የመስጠቱ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
ስልጠናው የኤሌትሪክ ተሽከርካሪዎች ከነዳጅ ተሽከርካሪዎች የተለዩ በመሆናቸውና ቴክኖሎጂውም አዲስ በመሆኑ የኤሌትሪክ መኪና ለሚያሽከረክሩ ባለሞያዎችና ባለድርሻ አካላት የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የስዊፍት ትራንስፖርት ቴክኒካል ማናጀር የሆኑት ኢሳያስ ግርማ ናቸው።
ሰልጣኞች በበኩላቸው ስልጠናው ከፅንሰ ሀሳብ በዘለለ በተግባር በመደገፉ በርካታ ዕውቀት እንዳገኙበት ጠቁመዋል።


